Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስታውቋል።
 
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን አገራዊ ፋይዳ ያለው ዘላቂ ተግባር አድርጎ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ ገልጸዋል።
 
ለዚህ ደግሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ አስፈላጊ በመሆኑ አገራዊ የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ያሉ ጉድለቶችን በመሙላት ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
 
በመሆኑም አገልግሎቱ ከዘመቻ ባለፈ ሕግና ሥርዓት ተበጅቶለት ተቋማዊ በሆነ መልኩ በዘላቂነት እንዲቀጥል ለማድረግ የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
 
የፖሊሲ ማዕቀፉም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰሩ የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚመሩበት እንደሚሆን ጠቁመው÷የበጎ ፈቃድ ሥራ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ለምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ እድገት ፣ ለሰላም ግንባታ እንዲሁም ለአገር ጠቀሜታ ያለውን ጉልህ ሚና በሚገባ እንዲወጣ ለማድረግ በፖሊሲ መመራቱ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
 
የሲቪል ድርጅቶችን የሚገድቡ ሕግጋት መሻሻላቸውን ተከትሎም በርካታ አገር በቀልና የውጭ ሲቪል ድርጅቶች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት 2ሺህ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ÷ ከዚህ በፊት 1ሺህ 800 አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሲቪል ድርጅቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
 
አሁን ላይ በድምሩ 3ሺህ 800 ድርጅቶች በፌዴራል ደረጃ ዕውቅና ተሰጥቷቸው በሥራ ላይ እንደሆኑ ነውየተናገሩት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.