Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የተቃጣውን የሳይበር ጥቃት ሙከራ መመከት ተችሏል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተለያዩ ግዙፍ ተቋማት የተቃጣውን የሳይበር ጥቃት ሙከራ መመከት መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው÷ በኢትዮጵያ የሁለተኛ ዙር የህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት መከናወኑ፣ አገራዊ ምርጫ መካሄዱንና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተካሄደው ህግ የማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
ጥቃቶቹ በአብዛኛው በግዙፍ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን ገልጸው እስካሁን ባለው ሂደት የጎላ ጥፋት ሳያስከትሉ መመከት መቻሉን ተናግረዋል።
የሳይበር ጥቃቱን መመከት ባይቻል ኖሮ በአገር ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ ሊያደርስ ይችል እንደነበርም ነው የተነገሩት፡፡
በሳይበር ደህንነነት ላይ በቂ ግንዛቤ ተይዞ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካልተደረገ በአገር ህልውና ላይ አደጋ ሊደቅን እንደሚችል አመላክተዋል።
ለአብነትም በኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም ብቻ በተለያዩ ተቋማት 2 ሺህ 800 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የሳይበር በይነ መረብ ቴክኖሎጂ ይዞት የመጣውን የእድገት አማራጭ መጠቀምና በዘርፉ ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት መቋቋም እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ለሳይበር ጥቃትና ደህንነት በቂ ጥንቃቄ ማድረግ ካልተቻለ በተቋማት ብሎም በሀገር ላይ አስከፊ አደጋ ሊከሰት ይችላል ብለዋል።
በመሆኑም የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ብቁ የሰው ኃይል፣ ጠንካራ የአሰራር ስርዓት እና በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እያንዳንዱ ዜጋ ለሳይበር ደህንነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸውም አንስተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እ.አ.አ በ2020 በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይበር ጥቃት 2 ነጥብ 5 ትሪሊየን የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ መድረሱን ጥናቶች የሚያሳዩ ሲሆን÷ በ2021 ደግሞ 6 ትሪሊየን የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል።
የሳይበር ደህንነነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.