Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ 129 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው፤ የ1 ሰው ህይወት አልፏል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 5 ሺህ 500 የላብራቶሪ ምርመራ 129 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 934 መድረሱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዛሬው እለት ባወጡት ሪፖርት አመላክተዋል።

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 124 ሰዎች ኢትዮጵያውያን፤ ቀረዎቹ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ፣ የአሜሪካ፣ የኤርትራ እና የሱዳን ዜጎች ሲሆኑ፥ እድሜያቸው ከ1 እስከ 90 ዓመት የሆኑ 75 ወንዶችና 54 ሴቶች ናቸው።

ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 101 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፥ 10 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 6 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 5 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 5 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣  1 ሰው ከሐረሪ ክልል እንዲሁም 1 ሰው ከጋምቤላ ክልል ናቸው።

በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት 19 ሰዎች (2 ከትግራይ ክልል፣ 6 ከአፋር ክልል፣ 1 ከሶማሌ ክልል እና 10 ከአዲስ አበባ) ያገገሙ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 281 መድረሱንም አስታውቀዋል።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ የአንድ የ80 ዓመት ሴት ኢትዮጵያዊ የአዲስ አበባ ነዋሪ ህይወት ማለፉንም ገልፀዋል። ሟቿ ወደ ሆስፒታል ለሌላ ህክምና በመጡ በአንድ ሰዓት ወስጥ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። በአስክሬን ምርመራም የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። በአጠቃላይ በቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 20 ደርሷል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ፤ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

በ24 ሰዓታት ውስጥ የተደረጉ የላቦራቶሪ ምርመራ ናሙናዎቹ ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወድስ የተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ136 ሺህ 868 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 934 ደርሷል።

አሁን ላይ 1 ሺህ 631 ሰዎች በህክምና ላይ ሲሆኑ፥ 281 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል፤ የ20 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 2 ሰዎች ወደ ሀገራቸው ጃፓን መመለሳቸው ይታወሳል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.