Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ 87 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው የ2 ሰዎች ህይወት አልፏል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 3 ሺህ 932 የላብራቶሪ ምርመራ 87 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 344 መድረሱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በዛሬው እለት ባወጡት ሪፖርት አስታውቀዋል።

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ እድሜያቸው ከ10 እስከ 70 ዓመት የሆኑ 59 ወንዶችና 28 ሴቶች ናቸው።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 41 ሰዎች የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት የሌላቸው፣ 28 ሰዎች የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው እንዲሁም 18 ሰዎች ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 67 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፥ 2 ሰዎች ትግራይ ክልል፣ 6 ሰዎች ኦሮሚያ ክልል፣ 7 ሰዎች አማራ ክልል፣ 4 ሰዎች ሶማሌ ክልል እንዲሁም 1 ሰው ሐረሪ ክልል ናቸው።

በሌላ መልኩ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ የሁለት ኢትዮጵያውያን ህይወት ማለፉንም ዶክተር ሊያ በሪፖርታቸው አስታውቀዋል።

የመጀመርያው የ30 ዓመት የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆን ሁለተኛዋ የ56 ዓመት በአዲስ አበባ የተጓዳኝ ህመም ክትትል ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው። ሁለቱ ግለሰቦች ህይወታቸው ያለፈና ለአስክሬን ምርመራ ወደ ሆስፒታል በመጡበት ጊዜ በተደረገ ምርምራ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ናቸው።

ይህንን ተከትሎም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 14 ደርሷል።

በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት 14 ሰዎች (6 ከኦሮሚያ ክልል እና 8 ከሶማሌ ክልል) ያገገሙ ሲሆን፥ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 231 ደርሷል።

በ 24 ሰዓታት ውስጥ የተደረጉ የላቦራቶሪ ምርመራ ናሙናዎቹ ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወስዶ የተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ116 ሺህ 309 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 344 ደርሷል።

አሁን ላይ 1 ሺህ 97 ሰዎች በህክምና ላይ ሲሆኑ፥ እስካሁንም 231 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል፤ የ14 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 2 ሰዎች ወደ ሀገራቸው ጃፓን መመለሳቸው ይታወሳል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.