Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ደህንነት ላይ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ላይ የሚያጋጥሙ የደህንነት ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ ያለመ ውይይት ተካሄደ፡፡

በመድረኩ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰንን ጨምሮ የኢትዮ -ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ እና የክልሎችና የከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የሀገሪቱን ወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍ ረገድ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለአንድ ሃገር ብሎም በባቡር መስመሩ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ በርኦ ሀሰን፥ በባቡር መሰረተ-ልማቶችና አገልግሎት ላይ በሚያጋጥሙ የደኅንነት ችግሮች የተነሳ መሰረተ-ልማቱ ለኢትዮጵያ ማበርከት የሚገባውን አስተዋጽኦ እንዳያበረክት ተግዳሮት እየሆነ ነው ብለዋል፡፡

በባቡር ዘርፍ እየተስተዋለ ያለውን ሕገ-ወጥ ተግባራት በመከላከል የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሻሻል በጸጥታውና በትራንስፖርት ዘርፉ ያሉ አካላት ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ይህ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮ -ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ በበኩላቸው፥ ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት በጭነትም ሆነ በህዝብ ትራንስፖርት ላይ ተጨባጭ አወንታዊ እድገት ማሳየቱን ገልፀዋል፡፡

በተለይ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ወሳኝ በሚባሉ የማዳበሪያ፣ ስንዴ እና ዘይት አቅርቦት ላይ ባቡሩ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ጠቁመው፥ በባቡሩ ምልልሰ ላይ የሚያጋጥሙ የውጭም ሆነ የውስጥ ተግዳሮቶችን በቅንጅት ለመፍታት እንዲህ ዓይነት የምክክር መድርክ ማዘጋጀት ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ድርሻ አለው ነው ያሉት፡፡

756 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር  665 ኪሎ ሜትሩ ኢትዮጵያ ውስጥ እና 91 ኪሎ ሜትሩ ደግሞ በጂቡቲ የሚገኝ ሲሆን ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ በአራት ክልሎች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር እና ሶማሌ እንዲሁም በሁለት የከተማ መስተዳድሮች አዲስ አበባ እና ድሬዳዋን እንደሚያቋርጥ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.