Fana: At a Speed of Life!

በኢንቨስተርነት ስም የማጭበርበር ወንጀል የሚፈጽሙ የውጭ ሀገር ዜጎች መኖራቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች ኢንቨስተር ነን በሚል ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል እንደሚፈፅሙ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ እንዳረጋገጠው÷ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች ኢንቨስተር ነን በሚል ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል በመፈፀም በዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ገልጿል።

መረጃው እንደሚያመለክተው በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሀብትና ንብረት ያላቸውን  ኢትዮጵያዊያንን ማንነት በጥናት በመለየትና ቀረቤታ በመፍጠር ከፍተኛ የሆነ የማጭበርበር ወንጀል እየፈፀሙባቸው መሆኑን  ማረጋገጥ ተችሏል።

እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የመጡ በማስመሰል፣  አብሯዋቸው የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንን እንደሚፈልጉ በማግባባትና ለስራ ማስኬጃም ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዳላቸው በመግለጽ ኢትዮጵያዊያንን ካገኙ አብሮ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ በማስመሰል  የሚያጭበረብሩ መሆናቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ አሳውቋል፡፡

እነዚህ አጭበርባሪዎች የኛ ዜጎች አብረዋቸው ቢሰሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማሳመን እና ከዚህ በተጨማሪም ዶላር የማባዛት ችሎታ እንዳላቸው በመግለፅ በተግባር አባዝቶ ለማሳየት መጀመሪያ የያዙትን ዶላር ሌላ ቦታ በፖስታ በመደበቅና ይባዛበታል ያሉትን ወረቀት ኬሚካል ውስጥ በመንከር ከዚያም የተነከረውን ወረቀት አውጥተው እንዲደርቅ በማድረግ በሌላ ፖስታ ውስጥ ያስቀመጡትን ትክክለኛ ዶላር በእጥፍ እንዳባዙት በማስመሰል ለሰዎቹ ያሳዩና ይበልጥ አመኔታን ለማግኘት ተባዛ ያሉትን ዶላር ባንክ ቤት ይዘው እንዲሄዱና ትክክለኛነቱን አረጋግጠው እንዲመጡ ካደረጉ በኋላ አሁን የተባዛውን ዶላር ትክክለኛ መሆኑን ስላረጋገጥን እስከ አንድ ሚሊየን ዶላር ይዛችሁ ኑና እናባዛ በማለት ወደ ማጭበርበር ተግባር እንደሚያስገቡ ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያን የብር ኖትም በእጥፍ ማባዛት እንደሚችሉ በማስረዳትና ሃብታም እንደሚሆኑ በማሳመን ዜጎች ያላቸውን ገንዘብ ይዘውላቸው ሲሄዱ ግማሾቹ ከነ ገንዘቡ ታፍነው ገሚሶቹ ደግሞ  እራሳቸውን ስተው እንደተገኙና ገንዘባቸውንም እንደተቀሙ ማረጋገጥ ተችሏልም ነው ያለው፡፡

የዚህ የማጭበርበር ወንጀል ሰለባዎችም ቤተሰቦቻቸው መበተኑን፣ ለድህነትና ለጤና መታወክ መዳረጋቸውን ማረጋገጡን የገለፀው ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ÷ ህብረተሰቡ ሁኔታውን ተገንዝቦ የማይገባ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ ለእንደነዚህ ዓይነት አጭበርባሪዎች ሲሳይ እንዳይሆን  አሳስቧል።

እንዲሁም ራሱንና ቤተሰቡን በመጠበቅ  አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥምም ህብረተሰቡ  በቅርብ ላሉ የፀጥታ አካላት ወይንም በነፃ የስልክ መስመር 987 በመደወል ጥቆማ መስጠት እንደሚችል አስታውቋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.