Fana: At a Speed of Life!

በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በቡድን በመደራጀት የዘረፋ እና የግድያ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 53 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በቡድን በመደራጀት የዘረፋ እና የግድያ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 53 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሃሰን ነጋሽ ÷ በከተማዋ የሚፈፀሙ የዘረፋ እና የግድያ ወንጀሎችን መነሻ በማድረግ እና የምርመራ እና የክትትል ቡድን በማቋቋም   በተደረገ እልህ አስጨራሽ እና አድካሚ ክትትል ወንጀሎቹን ሲፈፅሙ የነበሩ 53 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር  መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ እጅግ አደገኛ እና ደጋጋሚ ወንጀል ፈፃሚዎች መሆናቸውን ከጣት አሻራ ሪከርዳቸው ማረጋገጥ እንደተቻለ ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነር ሃሰን ከእነዚህም መካከል ለ55 ፣ ለ30 እና ለ10 ጊዜ የወንጀል የጣት አሻራ ሪከርድ የተመዘገበባቸው መገኘታቸውን ተናግረዋል ፡፡

በአራት ቡድን የተደራጁ 36 ተጠርጣሪዎች በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ባንክ ቤትን ጨምሮ በተለያዩ መኖሪያ ቤቶች ላይ ጥናት በማድረግ  እና በተሽከርካሪ በመንቀሳቀስ የዘረፋ ወንጀል ሲፈፅሙ ቆይተዋልም ነው ያሉት፡፡

እነዚህ የወንጀል ቡድኖች የሚጠቀሙባቸው 4 ሽጉጦች ፣ የካዝና መሰርሰሪያ  እና ለወንጀል ተግባራቸው የሚገለገሉባቸው ሌሎች ቁሳቁሶች እና ተሽከርካሪዎች ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ሙሉ በሙሉ ሊያዙ መቻላቸውን እና 14 የምርመራ መዝገብ እንደተደራጀባቸው ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ወርቅ ቤቶች ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው በተለይም ፒያሳ አካባቢ የዘረፋ ወንጀል የሚፈፅሙ በሁለት ቡድን የተደራጁ 9 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋልም ነው ያሉት፡፡

እንደ ምክትል ኮሚሽነር ሃሰን ገለፃ እነዚህ ተጠርጣሪዎች ወንጀል ለመፈፀም የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው እና የጦር መሳሪያ ታጥቀው በተሽከርካሪ እየታገዙ የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ በክትትል የፖሊስ አባላት ብርቱ ጥረት ሁሉም ተጠርጣሪዎች ከዘረፉት በርካታ ወርቅ፣ ለወንጀል ተግባራቸው ከሚገለገሉባቸው ተሽከርካሪ፣ሽጉጥ እና የፀጥታ አካላት የደንብ ልብስ ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም ፌሮ ብረት ፣ዱላ፣ ድንጋይ እና ስለት በመጠቀም ንብረት ለመውሰድ በሰው አካል ላይ ጉዳት ሲያደርሱ እና የግድያ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ በሁለት ቡድን የተደራጁ 8 ተጠርጣሪዎችም በከፍተኛ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተለይም በየካ ክፍለ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በለሊቱ ክፍለ ጊዜ አሳቻ ሰዓት እና ቦታ እየመረጡ ወንጀሉን ሲፈፅሙ ነበር፡፡

ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው አምነው የት እና እንዴት እንደፈፀሙም ለፖሊስ መርተው አሳይተዋል፡፡

ለዚህ ውጤት መገኘት የኮሚሽኑ የምርመራ እና የክትትል አባላት ከከፈሉት መስዋዕትነት በተጨማሪ ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት ላደረገው ትብብር  ምክትል ኮሚሽነር ሃሰን ምስጋናቸውን አቅርበው የከተማዋን ሠላም ይበልጥ አስተማማኝ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.