Fana: At a Speed of Life!

በከተማ ደረጃ የይቅርታ ቀን ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በከተማ ደረጃ የይቅርታ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ፕሬዚዳንቷ የይቅርታ ዝግጅቱ ወቅታዊ እና አስፈላጊ ነው ፤ ይቅርታ በመደራረግ ማህበራዊ እሴቶቻችንን በማጎልበት አብሮነታችንን እናጽና ብለዋል፡፡

አገር ያለ ሰው ምንም ነው ፤ ሰውም ያለ እሴት ባዶ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለማንነታችን መሠረት የሆኑ እንደ ይቅርታ ያሉ እሴቶቻችንን በማጎልበት ለነገው ትውልድ የምትሆን ፍቅር ፣ ሰላም እና አብሮነት የሰፈነባት የተሻለች ሃገር እንገንባ ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ የተሻለ ነገን ለመገንባት ከጥላቻ ፍቅርን ፣ ከመራራቅ መቀራረብን ፣ ከልዩነት አብሮነትን በማዳበር ይቅርታን ባህል በማድረግ ለሰላም ፣ ለአንድነት እና ለፍቅር መሠረት እንዲጥል የሃይማኖት አባቶቹ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የ2012 ዓ.ም በይቅርታ፣ በአብሮነት፣ በአምባሳደርነት ፣ በምስጋና እና በብሩህ ተስፋ ብስራት እንሻገር ያሉ ሲሆን ይቅር ብለንና ይቅርታን ተቀብለን አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ እንቀበልም ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ወጣቶች ለሃይማኖት አባቶችና ለመላም የከተማችን ነዋሪ የይቅርታ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአርበኞች ማህበር ተወካዮች ፣ የከተማዋ ወጣቶች ፣ የጸጥታ አካላት ፣ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ፣ የሃገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ የእግር ኳስ ደጋፊዎች እርስ በእርስ እና መላውን የከተማዋን ነዋሪ ይቅርታ መጠየቃቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.