Fana: At a Speed of Life!

በከተሞች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ኦንላይን መከታተል የሚያስችል ስርዓት ሊዘረጋ  ነው

አዲስ አበባ፣ጥር 5፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በከተሞች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ኦንላይን መከታተል የሚያስችል ስርዓት ሊዘረጋ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ይህም የከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም አካል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም አሰራር ስርዓትን ለማዳበር የስራ አመራር መረጃ ስርዓት ጥናት በአማካሪዎች  ማስጠናቱን አስታውቋል፡፡

ጥናቱን  ስራ ላይ ለማዋል የከተማ ባለሙያዎች፣ ክልሎች እና የፌዴራል ተንቀሳቃሽ ቡድን አባላትና  ሌሎች  ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት አውደ ጥናት ተካሂዷል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በሚኒስቴሩ የመሬት ልማትና ፕላን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዜር ገ/እግዚአብሔር እንደተናገሩት÷ ፕሮግራሙ ተግባራዊ በተደረገባቸው ባለፉት ዓመታት በከተሞች ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታው አያይዘውም ÷ ፕሮግራሙ የከተሞችን አቅም በገቢ መሰብሰብ፣ በፋይናንስ አስተዳደር፣ አሳታፊ የሆነ ዕቅድ በማዘጋጀት፣ የመፈፀም አቅምን በማሳደግ እና የመሠረተ ልማት አቅርቦትን በማሻሻል ከጊዜ ወደ ጊዜ በከተሞች በርካታ ለውጦች እንዲመዘገቡ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን የፕሮግራሙ እንቅስቃሴ ቴክኖሎጅ ተኮር ባለመሆኑ በፕሮግራሙ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን በየጊዜው መከታተልና ወቅቱን የጠበቀ ትክክለኛ መረጃ መለዋወጥ ባለመቻሉ በመረጃ ልውውጡ ላይ ክፍተቶች እየተፈጠሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የከተሞች ገቢ ማሻሻያ ፈንድ ሞቪላይዜሽንና ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ አምላኩ አዳሙ በበኩላቸው÷ በፕሮግራሙ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እና በከተሞች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ዘመናዊነት የተላበሰ አሰራር እንዲከተሉ ለማድረግ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም  ከችግሮች በመነሳት የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም ሶፍትዌር ወይም ሲስተም ለማልማት የዲዛይን ስራውን የሚያከናውን የውጭ አማካሪ መቀጠሩንም ተናግረዋል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አይ.ቲ ቢሮ የሚመራ ከኢትዮጵያ መረጃና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና ከሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር የተውጣጣ ቴክኒካል ኮሚቴ መቋቋሙንም ገልፀዋል፡፡

ሃላፊው በወርክሾፕ ላይ የተገኙትን ግብዓቶች በማካተት በቀጣይ ወደ ሲስተም ማልማት ስራው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ሲስተሙ የሚዘረጋበት ዋና አላማ  በአብዛኛው የነበረውን የሪፖርት ቅብብሎሽና የሚገጥመውን የሪፖርትና የቁጥር አለመጣጣም ለማስቀረትና  ወደ ቀልጣፋና ጊዜ ቆጣቢ  የአሰራር መንገድ ለመተግበር  መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

ሲስተሙ ከከተማ እስከ ፌዴራል ድረስ የሚዘረጋ ሲሆን ከእቅድ ጀምሮ እያንዳንዱ ከተማ የያዛቸው ፕሮጀክቶች ብዛት ፣  የአፈፃፀም ደረጃቸው ፣ የሪፖርቲንግ ስርዓት  በተለይ የከተማ ምክር ቤቶች፣ የክልል ምክር ቤቶች አስፈፃሚውን ሃይል እየተቆጣጠሩ የፕሮጀክቱንም አፈፃፀም ኦንላይን እያዩ አቅጣጫ ለማስቀመጥና ውሳኔ ለመስጠት ብሎም በቀላሉ ስራን ለማከናወን ያስችላልም ተብሏል፡፡

ሲስተሙ ሲለማ በዋናነት በ117 ከተሞች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ከፌዴራል እስከ ክልል የተደራጀ የመረጃ ስርዓት ከመፍጠር ባለፈ  በአይ.ቲ ዘርፍ  ለተመረቁ  ምሩቃን የስራ እድል እንደሚፈጥር ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር  ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.