Fana: At a Speed of Life!

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ለማዘመን ያለመ መርሃግብር ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የመረጃ አያያዝ ስርዓት ለማዘመን ያለመ መርሃግብር ይፋ ሆነ።

መርሃ ግብሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚቆይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ÷የመርሃግብሩ ማስጀመሪያ ስነስርዓትም ከ500 በላይ የዩኒቨርስቲዎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ከሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፣ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመረጃ አያያዝ ስርዓታቸውን በማዘመን እና መረጃን በአግባቡ ተደራሽ በማድረግ ተምሳሌታዊ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ውስጥ የሚከናወኑ ስራዎችን መረጃ በአግባቡ ከሽኖ በዘመናዊ መንገድ መያዝ እንዲሁም ለሚመለከተው ክፍል በየደረጃው ማስተላለፍ ሊለመድ የሚገባ ባህል መሆን አለበትም ነው የተባለው።

በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች የተማሪዎችን ቁጥር ሳይቀር ያለው መረጃ በጣም የተዛባ መሆኑ ተጠቁሞ÷ ይህ ደግሞ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝን ስርዓት አለመከተልንና ለመረጃ ጥቅም ትኩረት መንፈግ ነው ተብሏል።

የመረጃ መዛባት የሀገርን ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ትስስርና ፖለቲካዊ ሁኔታን በእጅጉ ከመጎዳቱም ባለፈ ለችግር መፍትሄ ሳይሰጥ ለመቆየት የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው ተመላክቷል።

መረጃ ተደራጅቶ ሲያዝ ግን የሀገር ሃብት ከመሆኑም ባለፈ ከየተቋማቱ የሚሰባሰቡ መረጃዎች ትክክለኛነት ለፖሊሲ አውጪዎች በእውነተኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ ችግር ፈቺ ፖሊሲዎችን እንዲቀርፁ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።

በመሆኑም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይንሳዊና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ተከትለው እንዲሰሩ ለማድረግ በማሰብ መርሃ ግብሩ ይፋ መሆኑን ከሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.