Fana: At a Speed of Life!

በካናዳ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ140 ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በካናዳ አልበርታ ግዛት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ140 ሸህ የካናዳ ዶላር በላይ ተሰበሰበ።

በካናዳ የተቋቋመው የጥምረት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአልበርታ ቻፕተር በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በአልበርታ ግዛት በካልጋሪ ከተማ፣ ኤድመንተን ከተማ፣ ሌትብሪጅና ፎርትማክመሪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማቀናጀት ባዘጋጁት የቨርቹዋል ኮንፈረንስ እና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በአንድ ቀን 142 ሺህ 900 የካናዳ ዶላር አሰባስበዋል፡፡

በግዛቱ ከዚህ ቀደም በተደረገ ገቢ ማሰባሰቢያ ከ25 ሺህ የካናዳ ዶላር በላይ በስጦታ መልክ መበርከቱ ተገልጿል።

በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉ የሚገኙት ተከታታይ የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴ የሚያኮራ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ከሚገኙ የጥምረት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቻፕተሮች ጋር በመተባበር እስካሁን በተካሄዱ 14 መድረኮች በስጦታ ብቻ ከ300 ሺህ  የካናዳ ዶላር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አብራርተዋል።

አምባሳደር ናሲሴ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሃገራቸው ያላቸው ፍቅር እና ለጋስነታቸው ታላቅ ዓርአያ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ  በአሁኑ ወቅት ካለችበት ውስብብ ሁኔታና የራሷን ተፈጥሮ ሃብት ተጠቅማ ዜጎቿን ከድህነት ለማላቀቅ የምታደርገውን ጥረት ለማሰናከል ከውስጥና ከውጭ ከተጋረጠባት ጫና አንፃር ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሃገሩ ጉዳይ ላይ አርበኛ በመሆን የሚያደርገውን ዘርፈብዙ ድጋፎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች በመድረኩ ላይ በመገኘት ኢትዮጵያውያን በዚህ ወሳኝ ጊዜ በፅናት አብረው በመቆም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ሙሌት እንዲሳካ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.