Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ለተገኘው አንፃራዊ ሰላም ባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶች ሚና የጎላ መሆኑ ተገለፀ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶች ሚና የጎላ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮው አስታወቀ።

በክልሉ በሚገኙ የሸካ፣ ምዕራብ ኦሞና ቤንች ሸኮ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ላለፉት ሦስት ዓመታት የጸጥታ ችግር መከሰቱን የቢሮው ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ አስታውሰዋል።

በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የህዝብ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት የቢሮ ሃላፊው፤ ባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶችን በመጠቀም ግጭቶችን መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች ሸፍተው ግጭት የመፍጠር ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላትን በሽምግልና ሥርዓት እንዲያግባቡ በማድረግ የተሰራው ሥራ ለተገኘው አንፃራዊ ሰላም ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡን በማወያየት በተሰራው ሥራ በምዕራብ ኦሞ ዞን ለሦስት ዓመት መንገድ ዘግተው ተለያይተው የነበሩ የሱሪና ዲዙ ወረዳ ነዋሪዎችን ወደ ቀድሞ አንድነታቸው መመለስ መቻሉን እንዲሁም ቴፒ ከተማ እና ጉራፈርዳ ወረዳ ላይ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት በተሰራው ሥራ አንጻራዊ ሰላም መታየቱን አመልክተዋል።

የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል በጫካ የሚገኙ ሽፍቶችን በሽምግልና አልያም በጸጥታ ኃይል የማስወጣት ሥራ ይከናወናል ማለታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው ክልሉ፥ ከመዋቅሩ በፊት የግጭት ቀጠና እንደነበር አስታውሰው ሕዝባዊ ውይይቶችና ባህላዊ የእርቅ፣ የሰላም ግንባታ እና የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ክልሉ የነበረበትን የግጭት ጫና መቀነስ ማስቻላቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጠል ክልሉ የጀመረው የባህላዊ የእርቅና የሰላም ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.