Fana: At a Speed of Life!

በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ 60 ሚሊየን ሰዎች ለከፋ ድህነት ይጋለጣሉ – የዓለም ባንክ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ዓለም ላይ 60 ሚሊየን ሰዎች ለከፋ ድህነት እንደሚጋለጡ አስጠነቀቀ።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ እንዳሉት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የበርካታ ሃገራት ኢኮኖሚ ተጎድቷል።

በወረርሽኙ ሳቢያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ስራ አጥ ሆነዋልም ነው ያለው ባንኩ።

ከዚህ ባለፈም የንግድ እንቅስቃሴዎች የተዘጉ ሲሆን ሁኔታው በታዳጊና ድህነት ውስጥ ባሉ ሃገራት የሚገኙ ዜጎችን ክፉኛ ጎድቷል ብሏል።

ፕሬዚዳንቱም ኮሮና ቫይረስ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ማመሰቃቀሉን እና የበርካታ ሃገራትን የጤና ስርዓት መጉዳቱን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም በዚህ አመት የዓለም ምጣኔ ሃብት በ5 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል ተናግረዋል።

ባንኩ 160 ቢሊየን ዶላር በእርዳታና አነስተኛ ወለድ ባለው ብድር መልክ ድሃ ሃገራት የቫይረሱን ተፅዕኖን መቋቋም እንዲችሉ አቅርቧል።

ይሁን እንጅ ይህ ድጋፍ እና ብድር ብቻውን በቂ አይደለም ብለዋል ፕሬዚዳንቱ ዴቪድ ማልፕስ።

ዓለም አቀፍ አበዳሪ አካላት ለድሃ ሃገራት የብድር እዳ ጫና ማቃለያ አለማድረጋቸው ደግሞ ሌላው ስጋት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በዓለም ባንክ ስሌት መሰረት አንድ ሰው በቀን ከ1 ዶላር ከ90 ሳንቲም ያነሰ ገቢ ካገኘ የከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛል ማለት ነው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.