Fana: At a Speed of Life!

በኮንሶ እና በአሌ አከባቢ ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 18 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮንሶ እና በአሌ አከባቢ ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ውይይት ተካሄደ፡፡

በውይይቱ የኮንሶ እና የአሌ ህዝቦች ለረጅም ዘመናት የዘለቀ አብሮነታቸውን በማስቀጠል እርስ በርስ እንደ አንድ የቤተሰብ አባል ሆነው መዝለቃቸው ተነስቷል፡፡

ይህ አንድነታቸው ያላስደሰታቸው አካላት ግን የግል ጥቅም እና ፍላጎታቸውን መሠረት በማድረግ የጸጥታ ችግር እንዲከሰት ምክንያት ሆነዋል ነው የተባለው፡፡

ዛሬ ግን የኮንሶ እና የአሌ ህዝቦች የቀደመ ሠላማቸውን ለማስቀጠል በየአካባቢያቸው  ያለውን የመተሳሰብ እና የመደጋገፍ ባህል ለማስቀጠል ውይይት በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡

በመድረኩ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው፣ የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

አቶ እርስቱ ይርዳው ህብረተሰቡን እርስ በእርስ በማጋጨት እና መሳሪያ በመሸጥ ሀብት ከሚያጋብሱ አካላት እራሱን መጠበቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የኮንሶና የኧሌ ህዝቦች እርቀ ሰላም በማስፈናቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ በእርሳቸው እና በክልሉ ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ይህ እርቀ ሰላም ኮንፈረንስ በኮንሶና በደራሼ ህዝቦችም መካከል ሊካሄድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

እንዲህ አይነቱ የሰላም ጥሪ በሌሎች አካባቢዎችም ፈጥኖ ሊተገበር እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

አሁን የተጀመረው ሰላም እንዲሰፍን የክልሉ መንግሥት በትኩረት ሲሰራ እንደነበርም አብራርተዋል፡፡

የኮንሶና የኧሌ ሽማግሌዎች እና አመራሮች ያከናወኑት አኩሪ ተግባር በሌሎች  የክልሉ አካባቢዎችም እንዲደገም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የኮንሶና የኧሌ ህዝቦች አንድ ሆነው ለዘመናት ቆይተዋል፡፡

ተሸናፊው የህወሀት ቡድን አጀንዳ አስፈጻሚዎች በፈጠሩት ችግር የአካባቢው ሰላም እንዲደፈርስ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በተፈጠረው ችግር እጃቸው አለበት ተብሎ የተጠረጠሩ 310 ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡

በሁለቱም ወገን ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን ወደ ህግ የማቅረብ ስራ ይሰራልም ብለዋል፡፡

በጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡

በሰላም ኮንፈረንሱ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኩታዬ ኩሲያ እና የኧሌ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማታማ ማጋ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ጠንካራ ትስስር ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ሁለቱ ህዝቦች መካከል ችግር ቢፈጠር እንኳ ለችግሮች መፍትሄ የሚሰጡበት ባህላዊ ዳኝነት እንዳላቸው ጠቅሰው የጎሳ መሪዎች እንደ አንድ የቤተሰብ አባል ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች መፍትሄ ሲሰጡ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪዎቹ በንግግራቸው እንደገለጹት የቀጠናውን ሰላም የማይፈልጉ ሀይሎች በፈጠሩት እኩይ አጀንዳ የሁለቱን ህዝቦች ዋጋ  ያስከፈለ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡

ከዚህ ቀደም የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት በመፍታት የኮንሶ እና የኧሌ ህዝቦች የቀደመ ቤተሰባዊ ትስስራቸው እንዲቀጥል የሰላም ኮንፈረንሱ ፋይዳው የጎላ እንዲሆን ያደርገዋልም ብለዋል፡፡

ችግሩ እንዲፈጠር ተዋናይ የነበሩ ሰዎችን በህግ እዲጠየቁ ይደረጋል ሲሉ ነው ዋና አስተዳዳሪዎቹ በንግግራቸው መጠቆማቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.