Fana: At a Speed of Life!

በወደብ የሚገኝ ከ10 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ስንዴ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በወደብ የሚገኝ ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና ተጨማሪ ስንዴ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን የባህር ትራንስፖረት አገልግሎት ድርጅትና የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቁ።

ተቋማቱ በጅቡቲ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በጣለ ዝናብ በአዲሱ ወደብ ውሃ በመግባቱና እና ባጋጠመ የማሽነሪ ብልሽት ምክንያት ማዳበሪያውም ሆነ ስንዴውን ማጓጓዝ ሳይቻል መቅረቱን አንስተዋል።

ሆኖም ያጋጠመውን ችግር በመፍታት ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና ተጨማሪ ስንዴ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት አመት ስንዴ ብቻ ከ1 ሚሊየን በላይ ቶን በድርጅቱ መጓጓዙን የገለፁት ኃላፊው፥ የፊታችን ሰኞ ተጨማሪ 600 ሺህ ቶን ስንዴ ወደ ወደብ እንደሚደርስ አስታውቀዋል።

አያይዘውም በዘንድሮ በጀት ዓመት የተከናወነ የገቢ ጭነት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ መሆኑንም አንስተዋል።

የፌዴራል ትራንስፖረት ባለስልጣን የዲሜሬጅና ሎጀስቲክ ዘርፍ ዳይሬክተሩ አቶ አበበ እሸቱ በአሁኑ ወቅት በመንግስት በኩል ባለ ቁርጠኝነት የተሽከርካሪ አቅርቦት ችግር የለም ሲሉ ገልፀዋል።

ያገጠመውን ችግር ለመፍታት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ፤ ክትትልም እየተደረገበት ይገኛል ብለዋል።

በታሪክ አዱኛ

 

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.