Fana: At a Speed of Life!

በወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ የተመራ የልዑካን ቡድን ከሱዳን መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ሚኒስትር እንዲሁም ከዘርፉ ተጠሪ ተቋማት ጋር መከረ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 12፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የተመራው የልዑካን ቡድን ከሱዳን መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ሚኒስትር እንዲሁም ከዘርፉ ተጠሪ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች ጋር መከረ።

ልዑካን ቡድኑ ከሱዳን መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ሚኒስቴር፥ እንዲሁም ከተጠሪ ተቋማት መካከል ከሱዳን የወደብ ባለስልጣን፥ ባቡር ትራንስፖርት፥ መንገዶች ባለስልጣን እና ከሱዳን ሀይዌይ ባለስልጣን እንዲሁም ከንግድ ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ባለስልጣን የሥራ ሃላፊዎችና ተወካዮች ጋር ምክክር አድርጓል።

ምክክሩ በዋናነት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በኩል ፖርት ሱዳንን በመጠቀም ሂደት ያጋጠሙ ማነቆዎችን በጋራ በመፈተሽ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችሉ ተግባራት ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን በሱዳን የኢፌዴሪ ኤምባሲ አስታውቋል።

ፖርት ሱዳንን ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የወደብ አማራጭ በማድረግ የሃገሪቱን የወጪ-ገቢ ንግድን ለማሳለጥና ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን በዚሁ ወደብ በመጠቀም ለሰሜንና ምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ጠቃሚ ውይይት ተደርጓል ነው የተባለው።

በተጨማሪም የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስትር ከሱዳን ማዕድን እና ኢነርጂ ተጠባባቂ ሚኒስትር ኽይሪ አብዱልራህማን ጋር በማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ በተለይም በነዳጅ ምርቶች አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በዚህም ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የነዳጅና ምርቶችን ከማጓጓዝ ጋር በተገናኘ እያጋጠሙ በሚገኙ ማነቆዎችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያም መክረዋል።

በሁለቱ ሃገራት ሊከናወኑ በሚችሉ የጋራ ፕሮጀክቶች እና ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውን የቤንዚን አቅርቦትን ለማሻሻል በመስኩ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጠናከር በሚረዱ የትብብር መስኮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.