Fana: At a Speed of Life!

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ስቡህ ገበያው በየጊዜው የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም በሦስት የመጠለያ ጣቢያዎች ከ89 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸው እና ከእነዚህ ውስጥም 16 ሺህ ተፈናቃዮች ብቻ በመጠለያ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የተፈናቃዮች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ቢሆንም የሚደረገው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን ነው የገለጹት፡፡ ለአብነትም ሁሉንም ተፈናቃዮች ሊያስተናግድ የሚችል በቂ የሆነ መጠለያም አለመሰራቱን አንስተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶችም ለአካባቢው ተገቢውን ትኩረት አልሰጡም ሲሉ ወቅሰዋል።
መንግስትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ብሎም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቀጣይ ዓመት ችግሩ ከአሁኑ የባሰ እንዳይሆን መጭው የክረምት ወቅት አርሶ አደሩ ወደ አካባቢው ተመልሶ ማሳውን እንዲዘራ ለማስቻል እና የመጠለያንም ጉዳይ እንዲሁ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት እንዲያስቡበት ነው የጠየቁት።
በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ምክንያት የዋግ ሕዝብ ከሀምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከአካባቢው መፈናቀሉን እንዲሁም ሀብትና ንብረቱን መዘረፉን ጠቁመው፥ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚገኙ የአበርገሌ፣ የፃግብጅና ወፍላ ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ፣ ዝቋላ ወረዳ በከፊል እና ከሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የተወሰኑ ቀበሌዎች አሁንም ድረስ በህወሓት ቁጥጥር ስር ናቸው ብለዋል።
በዚህም የመንግስት ተቋማትን እና የግለሰብ ንብረት እያቀጠለና እየዘረፈ እንዲሁም ሕዝቡን እያሰቃየ መሆኑን ከዋግ ኽምራ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.