Fana: At a Speed of Life!

በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በጋራ የሚተገበር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በጋራ የሚተገበር 3 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በጀት የተያዘለት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

በኮሚሽኑ አዳራሽ በተካሄደ የፊርማና ፕሮጀክቱን ይፋ ማድረጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው ፕሮጀክቱ በአባይ ንዑስ ተፋሰስ በሆኑት በጉደር፣ ሙገርና ጀማ ንዑስ ተፋሰሶች ውስጥ የሚተገበር ነው።

የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፥ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት፣ ሥራ ለመፍጠርና ምርታማነትን ለማሳደግ ፣የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ መጠንን ከፍ ለማድረግ እንደሚጠቅም ገልፀዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥምረት የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ዶክተር ቬራ ሴንግዌ በበኩላቸው፥ ፕሮጀክቱ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራና እንዲሁም ለነዋሪዎች በተለይም ለሴቶች የተለያዩ አማራጮችን በማመቻቸት ኑሯቸውን ለማሻሻል የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት “ተፈጥሮን መሠረት ያደረጉ መፍትሔዎች ለኢትዮጵያ የውሃ መሠረተ ልማት ጥበቃና የማኅበረሰብ አቅም ግንባታ” በሚል መሪ በመጪዎቹ 3 ዓመታት የሚተገበር መሆኑን ከውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ፕሮጀክቱ የሀገር በቀልና የውጭ ሀገር የዛፍ ዝርያዎችን በመትከልና በመንከባከብ፣ የአካባቢ ሥነ ምህዳርን በመጠበቅ፣ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎችን በማካሄድ የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ በማደረግና የውሃ መሠረተ ልማቶች፣ የአካባቢ ሥነ ምህዳሮችንና ማህበረሰቡ ተግዳሮቶችን የመቋቋም አቅም በመገንባት ለነዋሪው የተለያዩ አማራጮችን በማመቻቸት ኑሯቸውን ማሻሻልን ታላሚ ያደረገ ነው።

በመርሐ ግብሩም መጨረሻ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቅጽር ግቢ ውስጥ የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና ዶክተር ቬራ ሴንግዌን ጨምሮ ሌሎች ተሳታፊዎች ችግኞችን ተክለዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.