Fana: At a Speed of Life!

በውጭ ሀገራት እየኖሩ የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች ከኢንተር ፖል ጋር በመነጋገር በቁጥጥር ስር ለማዋል ይሰራል-የፌደራል ፖሊስ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ሀገራት እየኖሩ ከጁንታው ጋር ተባባሪ በመሆናቸው የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ጋር በመነጋገር በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚሰራ የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

በፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፋንታ ዛሬ በመቐለ ከተማ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ምክትል ኮሚሽነር በዚህን ወቅት ጁንታው ከተሞችን ለቆ ከመሸሹ በፊት በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የነበሩ ወንጀለኞችን መሳሪያ አስታጥቆ በመልቀቅ በከተሞች አካባቢ ዝርፊያ እንዲፈጽሙ ማድረጉን ነው የገለጹት።

ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በህግ የሚፈለጉ ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል።

በእስካሁኑ ሂደት በቁጥጥር ስር የዋሉና በቅርበት ክትትል እየተደረገባቸው ያሉ ተፈላጊዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ አስፈላጊው ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ መረጃው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ሁሉንም የጁንታው አባላትን ለመያዝ አሁንም ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በውጭ ሀገራት እየኖሩ ከጁንታው ጋር የወንጀል ተባባሪ በመሆናቸው የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ተጠርጣሪዎች ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ጋር በመነጋገር በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚሰራም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የፌደራል ፖሊስ በክልሉ ትልልቅ ከተሞች ተልዕኮ ወስዶ ወደ ስራ መግባቱንም ነው ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ ያስታወቁት።

“በክልሉ መደበኛ የፖሊስ ሥራ ለማስጀመርም የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች መቀሌ ገብተዋል” ብለዋል።

መኮንኖቹ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ከዚህ በፊት መመሪያን ብቻ አክብረው ሲሰሩ የነበሩ የክልሉ ፖሊስ አባላትን በህዝብ በማስተቸት መደበኛውን የፖሊስ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያደርጉ መሆኑንም አመልክተዋል።

በክልሉ የሚኖሩ በርካታ ዜጎች የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለው የጦር መሳሪያዎችን እየመለሱ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ፍተሻዎችን በማካሄድ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደሚሰራም ጨምረው ገልጸዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ የፌደራል ፖሊስ እያከናወነ ያለውን ተግባር በመደገፍ የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለህብረተሰቡ ምስጋና አቅርበዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.