Fana: At a Speed of Life!

በዓለም ላይ በአንድ ቀን ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ተመዘገበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለማችን ላይ በ24 ሰዓት ውስጥ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር መመዝገቡን የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት በትናንትናው እለት ብቻ በዓለማችን ላይ 106 ሺህ አዲስ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ተመዝግቧል።

ይህም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ ከተከሰተ ወዲህ ከፍተኛ መሆኑንም ነው ድርጅቱ ያስታወቀው።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በሰጡት መግለጫም፥ “አሁንም በዚህ ወረርሽኝ ውስጥ ረጅም መንገድ ይጠብቀናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ላይ ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑንም ዶክተር ቴድሮስ ገልፀዋል።

በተያያዘ ዜና በዓለም ዙሪያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ5 ሚሊየን መሻገሩን በዛሬው እለት ተገልጿል።

የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያመለክተው እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም ላይ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 5 ሚሊየን 33 ደርሷል።

በዓለም ዙሪያ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 329 ሺህ የደረሰ ሲሆን፥ 1 ሚሊየን 899 ሺህ 350 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ማገገማቸውንም ዩኒቨርሲቲው ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.