Fana: At a Speed of Life!

በዓመት ከ10 ሺህ ቶን በላይ የፕላስቲክ ቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል ኩባንያ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሊሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓመት ከ10 ሺህ ቶን በላይ የፕላስቲክ ቆሻሻ እንደገና ጥቅም ላይ ማዋል የሚችል ኩባንያ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመስራት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
“ኩቢክ ኢትዮጵያ” የተሰኘውና መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የፕላስቲክ አምራች የግል ኩባንያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ ለመስራት እና በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ የማምረቻ ሼድ በኪራይ ለመውሰድ የሚያስችለውን ስምምነት ነው ዛሬ የተፈራረመው፡፡
ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ እና የ“ኩቢክ ኢትዮጵያ” የፕላስቲክ አምራች የግል ኩባንያ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም አስፋው ተፈራርመውታል፡፡
በዚሁ ወቅት አቶ ሳንዶካን ደበበ እንደገለጹት ስምምነቱ÷ ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አካታች ለማድረግ እየሰራ ያለው ስራ ውጤት ማምጣቱን ማሳያ ነው፡፡
ኢንቨስትመንቱ አካባቢን ከብክለት ነፃ ለማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል።
በቀጣይ ኢንቨስትመንቱን ለማስፋፋት ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸው÷ ኩባንያውም በፍጥነት ወደ ስራ በመግባት ሌሎች ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን ታሳቢ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የ“ኩቢክ ኢትዮጵያ” የፕላስቲክ አምራች የግል ኩባንያ አስፈፃሚ አቶ ቅዱስ አስፋው በበኩላቸው፥ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣውን ኢንቨስትመንት ወደ ስራ ለማስገባት ስራዎችን በፍጥነት እናከናውናለን ብለዋል።
ኢንቨስትመንቱ በዓመት 125 ሺህ ሜትሪክ ቶን የካርበን ልቀትን መቀነስ የሚያስችል እና ለግንባታና የሪል ስቴት ገበያው በተመጣጣኝ ዋጋ የግንባታ ቁሳቁስ ለማቅረብ እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡
ከ10 ሺህ በላይ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የስራ እድሎችን እንደሚፈጥ ከኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.