Fana: At a Speed of Life!

በዓመት ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ሊያሳጣ በሚችል የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮምን በዓመት ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ሊያሳጣ በሚችል የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል በሚፈፀምባው ቦታዎች ላይ ጥብቅ የመረጃና የክትትል ሥራዎች ሲሰራ መቆየቱን አስታውሷል።

በዚህም በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ አራት እና ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት በተካሄደ ዘመቻም በህገ ወጥ መልኩ ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችን በመጥለፍ በራሳቸው መስመሮች ለደንበኞች በማቅረብ ህገወጥ ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩ ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉን አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከኢትዮ ቴሌኮም እውቅና ውጪ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችን በማስተላለፍ የራሳቸውን ገቢ ሲሰበስቡ መቆየታቸውንም ገልጿል።

ህገ ወጥ ድርጊቱ ባይከሽፍ ኢትዮ ቴሌኮምን በዓመት ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ሊያሳጣው እንደሚችልም ተገልጿል።

በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠሩት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፥ ሲገለገሉባቸው የነበሩ 10 ጌትዌይ (ሲምቦክስ)፣ 17 ቲፕሊንክ ፣ 59 ሲዲ ኤም ኤ፣ 3 ራውተር ፣ 2 ሺህ ሲም ካርድ፣ 3 ላፕቶፕ፣ የባንክ ደብተሮች፣ ሲፒኦዎችና ሌሎች ህገ ወጥ መሳሪያዎች በኤግዚቪትነት መያዛቸውንም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ህገ ወጦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በነበረው ሂደት ህብረተሰቡ ላሳየው የላቀ ተሳትፎ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ምስጋናውን አቅርቧል።

በቀጣይም ህገወጦችን በማጋለጥ ረገድ ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.