Fana: At a Speed of Life!

በዘመናት የተገነባውን የህዝቦች መተማመን ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶችን ኢትዮጵያውያን ሊያስተውሉ እና ሊያከሽፉ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘመናት የተገነባውን የማኅበረሰብ ሐብት በመናድ በህዝቡ ውስጥ መተማመን እንዳይኖር የሚደረጉ ጥረቶችን ማኅበረሰቡ ቆም ብሎ አንዲያስተውል እና እንዲያከሽፍ ምሁራን ጥሪ አቀረቡ፡፡

የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ደጉ አስረስ÷ መንግስት ፍትህን በማስፈን ዜጎች የሐብትና የሥልጣን ክፍፍል እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመሥራት መገፋፋቱ ሥፍራ እንዳያገኝ እና ጽንፍ-ረገጥ ዕሳቤዎች እንዳይስፋፉ መስራት አለበት ብለዋል፡፡

አክለውም ብዙሃኑን በጽንፈኝነት ውስጥ ማካተት በማይሆን ሚዛን ላይ ማስቀመጥ መሆኑን አስረድተው ከዛም ከዚህም የሚሰማው ጩኸት የጥቂቶች እንደሆነ በማስተዋል በሠላም የሚኖረው ህዝብ እንዳይረበሽ ጥንቃቄ  ሊወሰድ ይገባል ነው ያሉት።

በዘመናት ውስጥ የተገነባውን የማኅበረሰብ ሐብት በመናድ በህዝቡ ውስጥ መተማመን እንዳይኖር የሚሠሩ ሥራዎችን ለማክሸፍ ጥረት ይጠይቃል የሚሉት ደግሞ÷ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ሱራፌል ጌታሁን ናቸው፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ÷ በአሁኑ ወቅት የውጭና የውስጥ ጠላቶች ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በኢትዮጵያ የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት እየተጣደፉ ነው።

እንደ ማህበረሰብ ከመሰል አጀንዳዎች እራስን መጠበቅ ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡

ማኅበረሰቡ እኔነትን የሚያገኑ ሃሳቦች ሲገጥሙት ለምን ብሎ መጠየቅ እና ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚጠበቅበትም አመላክተዋል።

በተለይም “እነሱ” እና “እኛ” የሚሉ የልዩነት ወሬዎቻቸውን ባለማስተናገድ ዓላማቸውን ማክሸፍ ያስፈልጋል፤ ለዚህም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በሃይማኖት ወንድይራድ

 

 

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.