Fana: At a Speed of Life!

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ከ500 ሚሊየን በላይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ይተከላሉ ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ500 ሚሊየን በላይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መሆናቸውን የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ።
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኃሳብ አመንጭነት “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ኃሳብ ላለፉት 3 ዓመታት ተካሂዷል።
በየዓመቱ 92 ሺህ ሄክታር የነበረውን የደን ውድመት መጠን ወደ 32 ሺህ ሄክታር ዝቅ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፥ የዘንድሮው አራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ ይጀመራል ተብሏል።
የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ እንደገለጹት÷ መርኃ ግብሩ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ያስችላል።
ይህም ዘላቂ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ጠቅሰው፥ ላለፉት ሦስት አመታት በተሰሩ ሥራዎች ተመናምኖ የነበረው የተፈጥሮ ኃብት እንዲያገግም መደረጉን ገልጸዋል።
መርኃ ግብሩ የተፈጥሮ ኃብት እንክብካቤ እንደ አንድ አጀንዳ ሆኖ በአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ልዩ ትኩረት እንደተሰጠውም ጠቁመዋል።
አሁን በመላው አገሪቱ ያሉት የችግኝ ጣቢያዎችም 120 ሺህ መድረሳቸውን ገልጸው÷ ይህም በሥራ ፈጠራ ረገድ በርካታ የሥራ እድልን መፍጠር የቻለ መሆኑን አመላክተዋል።
አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎና አፕል በዋናነት ለምግብነት ከሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በዘንድሮው የችግኝ ተከላ የሚተከሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህ ችግኞች በቀጣዮቹ አመታት እራስን በምግብ ከመቻል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እንደሚያሳድጉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅቱ ለችግኝ ተከላ ምቹ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አደፍርስ÷ ኅብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ያሳየውን መነቃቃት እንዲደግመው ጠይቀዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.