Fana: At a Speed of Life!

በዝናብ እጥረት ምክንያት በተከሰተ ድርቅ ለችግር መጋለጣቸውን የቦረና ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዝናብ እጥረት ምክንያት በተከሰተ ድርቅ ለውሀ፣ለምግብና ለጤና ችግር መጋለጣቸውን የቦረና ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።

በዞኑ በ2013 ዓ.ም የበልግ ዝናብ በቂ አለመሆኑና የ2014 ዓ.ም የመኸር ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ ምክንያት በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑንም የቦረና ዞን አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሬባ ኦዳ ገልፀዋል።

በደረሰው ድርቅም 539 ሺህ 679 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የውሀ እጥረት እንዳጋጠማቸው የገለፁት ሀላፊው÷ ከዚህም ውስጥ 177 ሺህ 553 ለሚሆኑት ብቻ በቦቴ ውሀ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

እስካሁን በደረሰው የምግብ እጥረትም 6 ሺህ 398 ህፃናት ፣9 ሺህ 78 እናቶችና 2 ሺህ 226 አዛውንቶች ላይ የጤና ችግር መታየቱ ገልፀዋል።

እስካሁንም ለ118 ሺህ 864 ሰዎች የምግብ እርዳታ የተደረገ መሆኑን የገለፁት ሀላፊው 166 ሺህ 136 የሚሆኑት ደግሞ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አንስተዋል።

በተከሰተው ድርቅም 7 ሺህ 540 ከብቶች የሞቱ ሲሆን÷13 ሺህ 641 የሚሆኑት ደግሞ በሰው ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ መሆኑ ተገልጿል።

እንስሳቶቹን ከአደጋው ለማትረፍም 2 ሚሊየን 463 ሺህ 214 ቤል ሳር ከመንግስት ተጠይቋል።

አሁን ላይ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች እንደቀጠሉ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት እና አሳሳቢነት አንፃር ግን በቂ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል ሁሉ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።

በሌላ በኩል ከ200 በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶችም ሮቶዎችንና በቂ ውሀ የሚፈልጉ መሆኑን የገለፁት አቶ ሬባ ÷በዞኑ በ2009 ዓ.ም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞ የነበረ መሆኑን ገልፀው በመንግስት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በህዝብ ትብብር ማገገም ተችሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

በትዝታ ደሳለኝ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.