Fana: At a Speed of Life!

በየመን በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ መንግስት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ ማቆያ እስር ቤት ላይ በተከሰተ የእሳት አደጋ በእስር ቤቱ ውስጥ በነበሩ እስረኞች ላይ የሞትና የቁስለት አደጋ እንደደረሰ በሙስካት (ኦማን) የሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።

የአደጋው መንስኤ የእሳት ቃጠሎ ሲሆን የቃጠሎው መነሻ ከየመን ተፋላሚዎች ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ፣ ምንያህል ሰዎች እንደተጎዱና ምን ያህሉ ኢትዮጵያውን እንደሆኑም በኤምባሲው በኩል እየተጣራ ሲሆን መንግስት በትኩረት እየተከታተለው ያለ ስለሆነ የተረጋገጠ መረጃ እንደደረሰ ይፋ የሚደረግ ይሆናል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደረሰው የእሳት አደጋ ምክንያት ለጠፋው የዜጎቻችን ሕይወትና ለደረሰው የአካል ጉዳት ከፍተኛ ሃዘን እንደተሰማው በመንግስት ስም እየገለጸ ፤ ጉዳቱን ያከፋውና ሙሉ መረጃም ለማግኘት አዳጋች ያደረገው ዜጎች በህገወጥ መንገድ ያደረጉት ጉዞ ስለሆነ እንደሆነ ይገነዘባል።

በመሆኑም ዜጎች ወደ ውጭ ሃገራት ጭምር በነጻና ሕጋዊ መንገድ የመንቀሳቀስ መብታቸው በሕገ መንግስቱ የተደነገገ መብት ቢሆንም በሕጋዊና ሕጋዊ መንገድ ብቻ ከሃገር ለመውጣት ቢሞከር መሰል አደጋዎችንና የዜጎቻችንን መብት ለማስከበር ይረዳል።

ከዚህ አንጻር መንግስት ከተለያዩ ሃገራት ጋር በዋናነትም ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጋር የተለያዩ የአሠሪና ሠራተኛ ውሎችን ተፈራርሟል፤ እየተፈራረመም ይገኛል።

ዜጎቻችን ለሥራ ጉዳይ ወደ ውጭ ሃገራት የሚያደርጉትን ጉዞ በዚህ ሕጋዊነትን በተላበሰ መስመር ቢወጡ ለራሳቸው ህይወትም ሆነ ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ያስችላል።

መንግስት ትናንት በሰንዓ በተከሰተው ክስተት የተጎዱ ዜጎቻችን በደረሰባቸው አደጋ የተሰማውን ልባዊ ሃዘን በድጋሚ እየገለጸና በአደጋው የተጎዱ ዜጎቻችንን ብዛትና የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ ክትትሉ የቀጠለ መሆኑን እየገለጸ ሙሉ መረጃው እንደደረሰው ለህዝብ የሚያሳውቅ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.