Fana: At a Speed of Life!

በየዕለቱ ከ300 በላይ የኮቪድ ታማሚዎች ወደ ጽኑ ህክምና እንደሚገቡ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በየቀኑ ኮቪድ-19 ከሚገኝባቸው ሰዎች ውስጥ ከ300 በላይ የሚሆኑት ጽኑ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው እና ከእነዚህ ውስጥ እስከ 50 የሚደርሱት የመተንፈሻ አካልን የሚረዳ ማሽን የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በኮቪድ የሚሞቱና ጽኑ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

በየቀኑ ቫይረሱ ከሚገኝባቸው ሰዎች ውስጥ ከ300 በላይ የሚሆኑት ጽኑ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ከ40 እስከ 50 የሚሆኑት ደግሞ የመተንፈሻ አካልን የሚረዳ ማሽን ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

በየቀኑ የሚገለጸው ቁጥር ምርመራ ከተደረገላቸው ውስጥ ብቻ ስለሆነ ትክክለኛውን ቁጥር አያሳይም ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፤ አሁን እየተመረመረ ያለው በቀን ከ4 ሺህ እስከ 5 ሺህ ሰው በመሆኑ ከሚመረመረው በሶስትና አራት እጥፍ ከፍ ቢደረግ ውጤቱ በተመሳሳይ ከፍ ማለቱ እንደማይቀር ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ቫይረሱ የሚገኘው በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች እንደነበረና አሁን ላይ ግን ከ900 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች እንደተገኙም ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ከተመረመረው ከሶስት እስከ አራት በመቶ ብቻ ቫይረሱ የሚገኝባቸው እንደነበርና አሁን ግን ከ10 እስከ 15 በመቶ በአንዳንድ ቦታዎች ላይም ከ30 እስከ 40 በመቶ ቫይረሱ እየተገኘ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከቫይረሱ ስርጭት አንጻርም የጤና ሚኒስቴር ለስድስት ወራት የሚቆይ ኮቪድ 19ን የመከላከል ንቅናቄ ያካሂዳል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ ያመላክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.