Fana: At a Speed of Life!

በዩናይትድ ኪንግደም ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና  ኤርትራዊያን በጋራ የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)  በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና  ኤርትራዊያን በጋራ የድጋፍ ሰልፍ ማካሄዳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም በለንደንና በስኮትላንድ በተካሄዱ የድጋፍ ሰልፎች በጠላቶቻችን ድብቅ ሴራ ምክንያት የብሄር ተኮር ጥቃት ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችንን ለመዘከር፣ ብሄርና ማንነት ተኮር ጥቃትን መንግስት እንዲያስቆም እንዲሁም ጥፋተኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡ ህዝባችንም ይህን ተገንዝቦ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡

የሰልፉ አስተባባሪዎች እንደገለፁት አንዳንድ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት እና መንግስታት እንዲሁም አንዳንድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተዛቡ መረጃዎችን እያወጡ መሆናቸውን አውግዘዋል በተለይ  በተለይም በትግራይ ክልል ከተካሄደው የህግ ማስከበር እርምጃን በመጠቆም፡፡

አክለውም በውጭ ያሉ የጁንታው ቡድን አባላት ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ከኢትዮጵያ ህዝብ በዘረፉት ገንዘብ የሎቢ ቡድኖችን በከፍተኛ ገንዘብ በመቅጠር፣ ደጋፊዎቻቸውን እና ግብረ አበሮቻቸውን በማስተባበር የኢትዮጵያንና ኤርትራን ስም ለማጠልሸት እና የዲፕሎማሲ ጫና ለመፍጠር እያደረጉት ያለውን ጥረት በጽኑ ተቃውመዋል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግዳብ ድርድርን በተመለከተ ሱዳንና ግብፅ የሚያደርጉትን ኢፍትሃዊ ድርጊት በማውገዝ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል ኢትዮጵያ የያዘችውን አቋም አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ሱዳን ዓለም አቀፍ ህግ በመጣስ የፈፀመችው ወረራ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልፀው÷ ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ፣ ስልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ መሆኑን አውቀው ማንኛውም አካል ከጥፋት እንዲቆጠብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው ሰላማዊ ወዳጅነት ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያላቸውን ጽኑ ምኞት ገልፀው ድጋፍ እንደሚሰጡም አረጋግጠዋል፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ኢትዮጵያና ኤርትራዊያን በተጨማሪም የሁለቱም አገሮችና ወዳጆች ተገኝተው በሁለቱም አገሮች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና መቆም እንዳለበትና ለዚህም ከሀገሮቹ ጐን እንደሚቆሙ ገልፀዋል፡፡

ሰልፈኞቹ በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለውን የተዛባ መረጃ መነሻ ያደረገ የስም ማጥፋት ዘመቻ በተመለከተ ለዩናይትድ ኪንግደም መንግስትና ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም በኢትዮጵያን እንታደግ ግብረ ሃይል ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ኮሚኒቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የድጋፍ ሰልፍ በአየር ላንድ ደብሊንና በሰሜን አየር ላንድ በኮቪድ ገደብ ምክንያት በዌቢናር በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት መካሄዱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት  ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.