Fana: At a Speed of Life!

በደሴ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ በስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ 31 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወደሙ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደሴ ከተማ ትናንት ሌሊት በደረሰው የእሳት አደጋ እስካሁን በተደረገው ማጣራት ስድስት ሰዎች ሲጎዱ፥ 31 የመኖሪያ እና የንግድ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ፖሊስ አረጋገጠ።

በደሴ ከተማ 1ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ክፍል ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ክብረት እሸቴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ቃጠሎው በንብረትና በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

በቃጠሎው ወቅት በደረሰ ፍንዳታ በስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን እና ሦስቱ ወዲያው ታክመው ሲወጡ ሌሎቹ ሦስቱ ደግሞ በህክምና ላይ እንደሚገኙም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በእሳት አደጋው ሰባት የድርጅት፣ 24 መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም በሙጋድ የገበያ ማዕከልና በሸዋ በር መስጂድ ላይ በእሳት አደጋው መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ረዳት ኢንስፔክተር ክብረት ተናግረዋል፡፡

የፖሊስ የምርመራ ቡድን ባደረገው አሰሳ፥ ከቃጠሎው በኋላ የከባድ መሳሪያ ቅሪት መገኘቱን እና በቀጣይም የውድመት መጠኑን እንዲሁም የአደጋውን መንስኤ የማጣራት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመው ÷ ተጎጅዎች በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህክምና እያገኙ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በደሴ ከተማ አስተዳደር የ1ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ጥላሁን ፈንታው ሌሊት ላይ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት የእሳት አደጋው መከሰቱን እና አደጋውም በደሴ እና በኮምቦልቻ ከተሞች የእሳት አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ እንዲሁም በህብረተሰቡ ትብብር መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሰብለ አክሊሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.