Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ፓስፖርት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ፓስፖርት ማግኘት የሚችሉበት አሰራር ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ፓስፖርት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን በቀላሉ ፓስፖርት ማግኘት የሚችሉበት አሰራር ተግባራዊ ሊሆን ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኢሚግሬሽን፣ የዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በኤጀንሲው ይሰራ የነበረውን የፓስፖርት አመልካቾች ዜግነት የማጣራት ስራ በሚሲዮኑ እንዲሰራ የሚፈቅድና ከዚህ ቀደም ፓስፖርት ለማውጣት ይፈጅ የነበረውን ጊዜ የሚያሳጥር መሆኑ ተገልጿል።

እንዲሁም የአመልካቾችን ያልተፈለገ ምልልስ እና እንግልት የሚቀርፍ አሰራር በኤምባሲው እንዲጀመር የሚያስችል ነው ተብሏል።

ሰነድ ሳይኖራቸው በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ ፓስፖርት እና ሊሴ ፓሴ ጠያቂዎች አገልግሎቶቱን ማግኘት እንዲችሉ የአሰራር መመሪያ ቁ.2-01/2010 ወጥቶ ከታህሳስ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይሁንና ይህ መመሪያ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ጠያቂዎች ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የተገልጋዮችን ፍላጎት ያላሟላና ዜጎችንም ላልተፈለገ እንግልትና ምልልስ የዳረገ አሰራር ሆኖ መቆየቱን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.