Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ አፍሪካ የጎርፍ አደጋ ያስከትለውን ከፍተኛ ጉዳት ተከትሎ ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ታወጀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ባለፈው ሳምንት በክዋዙሉ-ናታል ግዛት የደረሰውን ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለ ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ከሀገሪቱ ካቢኔ ጋር የጎርፍ አደጋውን አስመልክቶ ውይይት ካደረጉ በኋላ ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መወሰኑን ትናንት ምሽት በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር አሰታውቀዋል።
አደጋውን የመቆጣጠር እና የማስተባበር ስራም የፌዴራሉ መንግስት ከሀገሪቱ የክልል መንግስታት እና ማዘጋጃ ቤቶች ጋር በጋራ የሚሰሩት ይሆናል ተብሏል፡፡
የአደጋ ጊዜ አዋጁ ቀደም ሲል የጎርፍ አደጋ በተከሰተበት በክዋዙሉ-ናታል ክልል መታወጁም ተመላክቷል፡፡
አዋጁ በሀገር አቀፍ ደረጃ መታወጅ ያስፈለገበት ምክንያትም የጎርፍ አደጋው ያስከተለውን ከፍተኛ ውድመት በክልል ደረጃ መቆጣጠር ከባድ በመሆኑ ነው ሲሉም ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ተናግረዋል፡፡
በዚህ የጎርፍ አደጋ በአፍሪካ በጣም ትልቁ እና በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚከወኑበት እንዲሁም ለደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ የጎላ ጠቀሜታ ያለው የደርባን ወደብ ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል ነው ያሉት ፕሬዜዳንቱ፡፡
ወደቡን ከቀሪው የሀገሪቱ ክፍል ጋር በሚያገናኘው መንገድ ላይም የጎርፍ አደጋው ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ የወደቡ መዳረሻ መቋረጡንም ነው ፕሬዜዳንቱ የገለጹት፡፡
ይህ አስከፊ የጎርፍ አደጋ ክዋዙሉ-ናታል ከ1987 እ.ኤ.አ ወዲህ ያስተናገደችው እጅግ የከፋው የጎርፍ አደጋ መሆኑም ተገልጿል።
በአደጋውም ከ440 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ እና ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
እንዲሀም ቤቶች፣ የንግድ ስፍራዎች፣ መንገዶች እና ድልድዮች ክፉኛ እንደወደሙ የሲጂቲኤን ዘገባ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.