Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል የሚነሳው የክልልነት ጥያቄ የሁሉንም ህዝቦች ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ይፈታል – አቶ ርስቱ ይርዳው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል የሚነሳው የክልልነት ጥያቄ የሁሉንም ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ እና ባከበረ መልኩ እንደሚፈታ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ከተለያዩ ዞኖች የሚቀርቡ በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች ፍትሃዊ፣ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ምላሸ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

ሰሞኑን ከክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ከህዝቡ ጋር በነበራቸው ውይይት ከክልል አደረጃጀት፣ ከመሰረተ ልማት እና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ችግሮችን በመፍታት የልማት ፍላጎትን በተግባር ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኑን አስረድተዋል።

አሁን ላይ ክልሉ ወደ ቀድሞ መረጋጋቱ መመለሱን ጠቅሰው፥ ህዝቡ ልማቱ ላይ በማተኮር አንድነቱን ለማጠናከር መስራት ይገባዋልም ነው ያሉት።

ክልሉ አሁን የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት መሰል የውይይት መድረኮች እንደሚቀጥል ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በየደረጃው መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ለውጡን ለማስቀጠል እንደሚሰራም አንስተዋል።

አያይዘውም ተፈናቃዮችን መልሶ ወደ መደበኛ ህይወታቸው የማቋቋሙ ስራ መቀጠሉን ጠቁመው፥ በጉራጌ ዞን ያለው አለመግባባት አለመፈታቱን አውስተዋል።

በዞኑ በማረቆና መስቃን ወረዳዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ከ20 ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

የዞኑ ነዋሪዎች ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ይመለሱ ዘንድ ላነሱት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እና ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከዞኑ አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አውስተዋል።

በሃይለእየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.