Fana: At a Speed of Life!

በድሬዳዋ በ150 ሚሊዮን ብር የተገነባው የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር በ150 ሚሊዮን ብር የተገነባው ሶዳ ኪንግ የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመርቆ ማምረት መጀመሩን የፋብሪካው አመራሮች ገለጹ።

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስፈጻሚና ባለድርሻ አቶ ሙሄዲን ፉክረዲን በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት በሀገራችን በአዮዲን እጥረት የሚከሰተውን የጤና ችግር ለመቅረፍ ጨውን ከአዮዲን ጋር የሚቀላቅል ፋብሪካ ተገንብቶ ማምረት ጀምሯል።

በቀን አንድ ሺህ 50 ኩንታል ጨው የሚያቀነባብረው ይኸው ፋብሪካ ለጊዜው ለ120 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተነግሯል።

ፋብሪካው በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ተጨማሪ የማስፋፊያ ግንባታ በማከናወን ላይ በመሆኑ የሥራ ዕድል የሚያገኙትን ዜጎች ቁጥር በእጥፍ ያሳድገዋል ብለዋል።

ፋብሪካውን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ እንደገለጹት ድሬዳዋን የምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካው የእዚሁ አካል መሆኑን ገልጸው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምጣኔ ሀብት በማጎልበት ገንቢ ሚና ይጫወታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ልዩና አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚያደርግም ምክትል ከንቲባው ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.