Fana: At a Speed of Life!

በድሬዳዋ ከተማ በከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ታቅፈው የነበሩ አባወራዎች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ታቅፈው የነበሩ ከ3 ሺህ በላይ አባወራ ተጠቃሚዎች ተመረቁ።

በከተማ ነዋሪዎች ላይ የሚስተዋለውን የምግብ ዋስት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ በሃገር አቀፍ ደረጃ በመተግበር ላይ በሚገኘው የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና የድሃ ድሃ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል።

ፕሮግራሙ እየተተገበረ ከሚገኝባቸው ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች መካከል በድሬዳዋ በሁለተኛው ዙር የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ታቅፈው የነበሩ 3 ሺህ 428 አባወራዎች ሽግግር በማድረጋቸው ከፕሮግራሙ ተመርቀው ወጥተዋል።

የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በሦስት ዓመት ቆይታቸው በደረቅ ቆሻሻ መሰብሰብና ማስወገድ፣በአረንጓዴ ልማት፣ በተፋሰስ ልማትና በመለስተኛ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የከተማ የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዳሬክተር አቶ ማርቆስ ባዩህ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የልየታ ስራ መሰራቱንና በአጠቃላይ በድሬዳዋ ከተማ በሦስት ዙር የሴፍትኔት ፕሮግራም ከ46 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የሁለተኛው ዙር ተጠቃሚዎች ከፕሮግራሙ ከመውጣታቸው በፊት የህይወትና የንግድ ክህሎት እንዲሁም የስራ ፈጠራ ስልጠና የተሰጣቸው በመሆኑ ከ61 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ በብድር እንደሚለቀቅላቸው አመልክተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ ቡህ የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ከ2009 ዓም ጀምሮ በአስተዳደሩ በሚገኙ ዘጠኝ የከተማ ቀበሌዎች ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን በሁለት ዙሮች 7 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን የኑሮ ሽግግር በማድረግ ራሳቸውን እንዲችሉ መደረጉን አስታውቀዋል።

ከሁለተኛው ዙር የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል በቀበሌ 02 ቀበሌ በገንደ ሀሎሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በ5 ሚሊየን ብር የተገነቡ ተጨማሪ የመማሪ ክፍሎች  ተመርቀዋል።።

በተሾመ ኃይሉ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.