Fana: At a Speed of Life!

በድርቅ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ፈጣን የድጋፍ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎችን በትኩረት መከወን ይገባል-አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ አካባቢዎች በሚስተዋለው የድርቅ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ፈጣን የድጋፍ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት ማከናወን እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡
 
የብሄራዊ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚቴ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፥ በአስቸኳይ ጊዜ የድጋፍ አሰጣጥ ሂደት አስፈፃሚ አካላት ያሳዩት ፈጣን ምላሽ እና ቅንጅታዊ አመራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
 
የብሄራዊ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚቴ ሰብሳቢ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ እንዳሉት፥ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚስተዋለው የድርቅ አደጋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ፈጣን የድጋፍ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል፡፡
 
ቀደም ባሉት ጊዜያት በአስቸኳይ ጊዜ የድጋፍ አሰጣጥ ሂደት አስፈፃሚ አካላት ካሳዩት የተቀናጀ ርብርብ በተሻለ ትኩረት የድርቅ አደጋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ፈጣን የድጋፍ ምላሽ ሊያገኙ እንደሚገባ አቶ ደመቀ አሳስበዋል፡፡
 
ብሄራዊ ኮሚቴው ባስቀመጠው አቅጣጫ በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አቅርቦት እና ስርጭት ሂደት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ዘላቂ በሆነ መልኩ በመፍታት የድጋፍ ምላሹ የመጨረሻ ተጠቃሚዎችን ማዕከል ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
 
ሃገሪቱ የገጠማትን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተቋቁማ እንድትሻገር የዳያስፖራው ማህበረሰብ ላደረገው ድጋፍ አቶ ደመቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
 
በቀጣይም በሁሉም አቅጣጫ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
የብሄራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በበኩላቸው÷ በብሄራዊ ኮሚቴ በሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች እና በሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች መሰረት የተጀመሩት የድጋፍ እና ምላሽ አሰጣጥ ስራዎች በሚታይ መልኩ ወደ መሬት መውረድ ጀምረዋል ብለዋል፡፡
 
ይሁንና ሃገሪቱ ከገጠማት ውስብስብ ችግሮች አኳያ ከአጋር አካላት የሚደረገው ድጋፍ በቂ በሚባል ደረጃ ባለመሆኑ ምክንያት ጅምር የድጋፍ እና ምላሽ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
 
በመጨረሻም የብሄራዊ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚቴ በአስቸኳይ ጊዜ የድጋፍ አሰጣጥ ሂደት አስፈፃሚ አካላት ያሳዩት ፈጣን ምላሽ እና ቅንጅታዊ አመራር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.