Fana: At a Speed of Life!

በድርቅ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ክልሎች የእንስሳት መድኃኒት ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በተከሰተው በድርቅ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው እንስሳት የሚውል የመድኃኒት ድጋፍ ተደረገ፡፡
ድጋፉ የተደረገው÷በግብርና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ እንስሳት ጤና ለገጠር ልማት ፕሮጀክት አማካይነት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በርክክቡ ላይ የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ÷ እንስሳቱ በሚፈለገው መልክ እራሳቸውን ከበሽታ እንዲከላከሉ፣ የታመሙትም እንዲታከሙና የአመጋገብ ስርዓታቸው እንዲስተካከል የሚረዱ መድኃኒቶች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
መድኃኒቶቹ የውስጥና የውጪ ጥገኛን ለመከላከል፣ በአንዳንድ ኢንፌክሽኖች የተጎዱ እንስሳትን ለመከላከል፣ የእንስሳትን የምግብ ፍላጎት የሚያሻሽሉና ቶሎ ተመግበው ሰውነታቸውን ወደ ቦታው እንዲመለስ የሚረዱ መድኃኒቶች መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡
ድጋፉን ያገኙት ክልሎች መድኃኒቶቹን በተገቢው መንገድ ለሚፈለግበት ቦታና ማህበረሰብ እንዲያደርሱና ግብርና ሚኒስቴርም ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ ድጋፎችን አጠናቅሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በኢትዮጵያ እንስሳት ጤና ለገጠር ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር መላኩ አሰፋ÷ በሁለቱ ክልሎች ድርቁ በከፋባቸው አካባቢዎች የሚሆን የተለያዩ የእንስሳት መድኃኒቶች ለአደጋ ጊዜ ከተፈቀደው በጀት ተገዝተው መከፋፈላቸውን ተናግረዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.