Fana: At a Speed of Life!

በድጎማ ለህብረተሰቡ የሚቀርበው የምግብ ዘይት የጥራት ደረጃ መሻሻሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣የካቲት 3፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት ድጎማ በማድረግ ከውጪ እያስገባ ለህብረተሰቡ ሲያሰራጨው የነበረው ፓልም የምግብ ዘይት የጥራት ደረጃ መሻሻሉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ፓልም የምግብ ዘይት መንግስት የዋጋ፣ የአቅርቦና የሥርጭት ቁጥጥር እያደረገባቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ከሚያቀርባቸው መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች አንዱ ነው።

ዘይቱ በውስጡ ካለው የስብ መጠን እና ከአስመጪዎች መረጣ ፍትሐዊነት ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች ሲነሱ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችና ውዝግቦችን ለመፍታት የምግብ ዘይት አቅርቦትና ስርጭት ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 020/2011 አውጥቶ ከታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ አድርጓል፡፡

በዚህ መሰረት ከዚህ በፊት ሲቀርብ የነበረው የፓልም የምግብ ዘይት ወይም በተለምዶ የሚረጋው ዘይት ሳይሆን ፓልም ኦሊን (palm olien) የተባለ ፈሳሽ የምግብ ዘይት መሆኑ በመመሪያው  መቀመጡ ተገልጿል፡፡

በፊት ይቀርብ የነበረው ፓልም የምግብ ዘይት የጥራት ደረጃ CES138:2015  የነበረ ሲሆን  ÷ አሁን የሚቀርበው ፓልም ኦሊን የምግብ ዘይት ተሻሽሎ CES245 የጥራት ደረጃ መስፈርቶችን አሟልቶ የተመረተና በቫይታሚን ኤ እና ዲ የበለጸገ መሆን እንዳለበትም መመሪያው ማስገደዱ ተብራርቷል፡፡

መመሪያው ከጥራት ደረጃ በተጨማሪ የዘይት አስመጪዎች ምልመላ፣ የዋጋ ትመና እና የትርፍ ምጣኔ አወሳሰንን የያዘ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ አቅራቢዎችን ለመመልመል በወጣው መስፈርት መሰረት በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ በሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት አማካኝነት አሳታፊና ግልፀኝነት ባለው መልኩ 24 የምግብ ዘይት አስመጪዎች ተመርጠው ወደ ስራ መግባታቸው ተገልጿል፡፡

በሌላም በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስገዳጅ የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃ የወጣላቸው የገቢ ምርቶች ላይ  ባደረገው የቁጥጥር ስራ  ከጥራት ደረጃ በታች የሆነ 19 ሺህ 770 ጀሪካን ፓልም የምግብ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ ሲል  መታገዱን ገልጿል፡፡

የቁጥጥር ስራው ከፓልም የምግብ ዘይት በተጨማሪ   የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣የአርማታ ብረት፣ ሳሙና፣ሚስማር እና የታሸጉ ምግቦች  ላይ መከናወኑ ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት 6 ወራት 875 ሺህ 691 ሜትሪክ ቶን የገቢ ምርቶች ላይ የጥራት ቁጥጥር ለማድረግ አቅዶ በ1 ሚሊየን 465 ሺህ 177  ሜትሪክ ቶን ምርቶችን ቁጥጥር ማድረጉን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.