Fana: At a Speed of Life!

በዶሃ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓትን ተግባራዊ የሚያደርገው በዶሃ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ተመርቋል።

ትምህርት ቤቱን የኳታር የትምህርት እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር መሃመድ ቢን አብደልዋህድ አል ሃማዲ እና በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች በይፋ መርቀውታል።

የትምህርት ቤቱ መከፈት በዶሃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሠ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ወላጆች ልጆቻቸውን በተመጣጣኝ ክፍያ እንዲያስተምሩ፣ ልጆች የሀገራቸውን ቋንቋ እና ባህል እንዲያውቁ ያስችላል ተብሏል።

እንዲሁም በከፍተኛ የትምህርት በወጪ እና በቋንቋ ምክንያት ልጆቻቸውን ወደ ሀገር ቤት ለትምህርት በመላክ ተራርቀው የሚኖሩ ቤተሰቦችን ችግር የሚያቃልል መሆኑም ተጠቁሟል።

አምባሳደር ሳሚያ በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የትምህርት ቤቱን መቋቋም በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በእውቀት እና በማስተባበር የደገፉትን የኳታር መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ መስሪያ ቤቶች እንዲሁም የመስራች ኮሚቴ አባላትን አመስግነዋል።

ትምህርት ቤቱ በሙሉ አቅሙ ሥራውን ሲጀምር ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ሁለተኛ ጀረጃ ትምህርት ቤት ለማስተማር የሚያስችሉ በቂ የመማሪያ ክፍሎች እንዳሉት በኳታር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

ትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሥራውን በመስከረም 2013 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ 2ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.