Fana: At a Speed of Life!

በጀርመንና ስፔን በተደረጉ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጀርመን፣ ፍራንክፈርት፣ ስፔን እና ቫሌንሽያ ከተሞች በተደረጉ የሩጫ ውድድሮች ድል ቀንቷቸዋል።

በፍራንክፈርት የማራቶን ውድድር ፍቅሬ በቀለ ሲያሸነፍ በቫሌንሽያ የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ሰንበሬ ተፈሪ ድል ተቀዳጅተዋል።

የፍራንክፈርቱን ማራቶን በሁለት ሰዓት ከሰባት ደቂቃ ከስምንት ሰከንድ በበላይነት ያጠናቀቀው ፍቅሬ በቀለ የሀገሩን ልጅ ዳዊት ወልዴን የቀደመው በሁለት ሰከንድ ብቻ ነው።

እንደ ወንዶቹ አንገት ለአንገት መተናነቅ ባልታየበት በሴቶቹ የማራቶን ሩጫ ኬንያዊቷ ቫላሪ አያቢ በሁለት ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ የስፍራውን ክብረወሰን በመስበር አሸንፋለች።

በሁለት ደቂቃ ወደ ኋላ የዘገየችው መገርቱ ከበደ ሁለተኛ ስትወጣ የአምናው የውድድሩ አሸናፊ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት መስከረም አሰፋ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በሌላኛዋ አውሮፓዊት ሀገር በስፔን በቫሌንሽያ ከተማ በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ በወንዶችና በሴቶች ምድብ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል።

ሰንበሬ ተፈሪ ውድድሩን በአንደኛነት ያጠናቀቀችው የርቀቱን የኢትዮጵያ ክብረወሰን በ13 ሰከንድ በማሻሻል ጭምር ነው።

ሰንበሬ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷን የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፋን ሀሰንን በማስከተል የገባችው በአንድ ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ከ32 ሰከንድ ነበር።

ባለፈው ወር መጨረሻ በዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1ሺህ 500 እና 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ድርብ ድል ያስመዘገበችው ሲፋን በ21 ሰከንድ ተቀድማ ሁለተኛ መውጣቷን ዶይቼ ቬለ ዘግቧል።

በዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው ዮሚፍ ቀጀልቻ በቫሌንሽያው ውድድር ድል ቀንቶታል።

በ59 ደቂቃ ከ05 ሰከንድ ውድድሩን የጨረሰው ዮሚፍ፥ ሁለተኛ የወጣውን ኬንያዊ በናርድ ንጌኖን የቀደመው በሁለት ሰከንድ ነው።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጀማል ይመር ሶስተኛ በመሆን በውድድሩ ኢትዮጵያውያን በበላይነት ደምቀው እንዲታዩ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.