Fana: At a Speed of Life!

በጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት እያደረገ ይገኛል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዲሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት እያደረገ ይገኛል።

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከአቡዳቢ አልጋ ወራሽ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ተገናኝተው ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተላከ መልዕክት አድርሰዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ እየተጠናከረ እንደመምጣቱ መጠን በሁለቱ አገራት የመከላከያ ተቋማት ያለው ግንኙነት በዚያው ልክ እየተጠናከረ፣ የትብብር አድማሱም እየሰፋ መሄዱን ጠቅሰዋል፡፡

ልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንም በበኩላቸው ከጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ አህመድ የተላከውን መልዕክት ከተቀበሉ በኋላ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት የሁለቱንም ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲሄድ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የአገራቱ ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በትምህርትና ቴክኖሎጂ፣ በደህንነትና ጸጥታ ዘርፍ፣ እንዲሁም በወታደራዊ ግንኙነቶች ይበልጥ እንዲጠናከር በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በኩል ያለውን ቁርጠኝነት በመጥቀስ የበኩላቸው ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከልኡል አልጋ ወራሽ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር በምስራቅ አፍሪካ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና በሀገራችን የትግራይ ክልል ስለተካሄደው የሕግ ማስከበር እርምጃና አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታም አብራርተውላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በመጪዎቹ ቀናቶች ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የመከላከያ ሚኒስትር እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.