Fana: At a Speed of Life!

በጅማ ከተማ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች የተገኘባቸው 26 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጅማ ከተማ ዛሬና ትናንት በተደረገ ፍተሻ የተለያዩ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች የተገኘባቸው 26 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን ዲቪዚዮን የሚዲያ ዘርፍ ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ገዛኸኝ አውግቸው ÷ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ትናንት ቤት ለቤት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሰባት የተለያዩ ሽጉጦች፣ 73 ጥይቶችና ሰባት የጥይት ካርታዎች ተገኝተዋል ብለዋል።
እንዲሁም አምስት ሲም ካርዶች፣ ህጋዊነት የሌላቸው አምስት ማህተሞች፣ አምስት የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎችና በርካታ ባለስለት መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።
በተመሳሳይ ዛሬ በተደረገ ፍተሻ ደግሞ ሶሰት የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ ሁለት ሽጉጦች፣ 108 ተተኳሽ ጥይቶችና አንድ የጦር ሜዳ መነጽር መገኘቱን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ሶስት የተለያዩ አገራት ፖስፖርቶች፣ አምስት የባንክ ሂሳብ ደብተሮችና 16 የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር መዋሉን ዋና ኢንስፔክተር ገዛኸኝ አስረድተዋል።
ህገወጥ መሳሪያዎችና ሌሎችም እቃዎች የተገኘባቸው 26 ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቀጣይም የፀጥታ ሀይሉና ሕብረተሰቡ ህገ ወጥ ተግባራትን ለማጋለጥ እያደረጉ ያሉት ትብብርና ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ዋና ኢንስፔክተሩ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.