Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መሰረቱ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ ስድስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊና ሌሎች ጉዳዮች ተቀራርበው ለመስራት የሚስችላቸውን የጋራ ምክር ቤት መስርተዋል ።

ፓርቲዎቹ የጋራ ምክር ቤቱን የመሰረቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ባመቻቸው መድረክ በቀረቡት የጋራ የመግባቢያ ሰነዶች ዙሪያ በመወያየት ከተፈራረሙ በኋላ ነው።

በክልል ደረጃ የጋራ ምክር ቤት ከመሰረቱት መካከል ጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ጋህነን/ ፣ ብልጽግና እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ ኢዜማ/ እና የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ/ጋህነዴን/ ይገኙበታል።

የጋራ ምክር ቤቱ ከሁሉም ፓርቲዎች በእኩል የተወከሉ 30 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ለቀጣይ ስድስት ወራት የጋራ ምክር ቤቱን የሚመሩ ዋና እና ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም ዋና ጸሐፊ በመምረጥ መሰየማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከምክር ቤቱ መስራቾች መካከል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ፤ ምክር ቤቱ በክልሉ ብሎም በሀገራዊ የጋራ ጉዳዮችና ሌሎች ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ምቹ አጋጠሚን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በተለይም የፈረሙት የመግባቢያ ሰነዶችን በማክበርና በማስከበር ረገድ ሁሉም ፓርቲ በአግባቡ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚጋባ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ የሚኖሩ የጋራ አጀንዳዎችና የሚጋጠሙ ችግሮች በጋራ ለመፍታት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ፒተር አማን ናቸው።

‘‘ለክልልችንም ሆነ ለሀገራችን ያለናት እኛው ስለሆነን እንደ ፓለቲካ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ በያገባኛል ስሜት የህግ የበላይነትን እያከበርን በጋራ ልንሰራ ይገባል’’ ብለዋል።

6ኛው ጠቅላላ ምርጫም ሰላማዊና ዴሞክራሲ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በጋራ መስራት እንደሚገባም አቶ ፒተር አመልክተዋል።

የጋህፍሰልዴን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቾል ኮር በበኩላቸው ፤የጋራ ምክር ቤቱ ሊያጋጠሙ የሚችሉ ችግሮች በጋራ በመወያየት መፍትሄ ለመሻት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢዜማ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ምክትል መሪ ኮማንደር ጋድቤል ቦል የጋራ የምክር ቤቱ የመግባቢያ ሰነዶች ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ስጋቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ባመቻቸው የፓርቲዎች የጋራ መድረክ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአሠራር ደንብ፣ የቃል ኪዳን ሰነድ ለማስፈጸም የመጣውን የስነ ስርዓት ደንብ ጨምሮ አራት የመግባቢያ ሰነዶች በአመራሮቹ ተፈርመዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.