Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህወሃት ውስጥ ያለ ቡድን በመከላከያ ላይ የፈፀመውን ጥቃት አወገዙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህወሃት ውስጥ ያለ ቡድን በመከላከያ ላይ የፈፀመውን ጥቃት አውግዘዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህወሃት ውስጥ ያለ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው ጥቃት አሳፋሪና የሀገርን ሉዓላዊነት አሳልፎ የሰጠ መሆኑን በመግለፅ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
ፓርቲዎቹም የጋምቤላ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት፣ ኢዜማ፣ የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ጋህነዴን) እና የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ጋህነን) ናቸው።
በጋራ ባወጡት ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰደ ያለው እርምጃ ሁሉም ዜጋ ሊደግፈው ይገባል ብለዋል፡፡
የህወሃት የጥፋት ቡድን የሀገሩን ዳር ድንበር ቀን ከሌሊት በመጠበቅ ላይ በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ካምፕ ላይ የፈፀመው ጥቃት ሀገርን የማፍረስ ተግባርና በሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ አሳፋሪ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የህወሃት ጽንፈኛው ቡድን አሰልጥኖ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባሰማራቸው የጥፋት ቡድኖች የተፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን በማውገዝ ቡድኑ በሽብር ወንጀል እንዲጠየቅ በአቋም መግለጫቸው ላይ አብራርተዋል፡፡
ትናንት የነበረው የጋምቤላና የትግራይ ህዝብ ወንድማማችነት ነገም የሚቀጥል መሆኑን በመግለጽ የትግራይ ህዝብ የህወሃት ጁንታን የጥፋት ዓላማ ተገንዝቦ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን እንዲቆም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደገፍ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ቡድኑ ተስፋ የቆረጠ የጥፋት ቡድን በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ባሰማራቸው ቡድኖች ጥቃት ሊፈጽም ስለሚችል የጋምቤላ ክልል ህዝብ ከፀጥታ አካሉ ጋር በመሆን አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅና ለፀጥታ ሀይሉ አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጥፋት ቡድኑ መሸሸጊያ ካደረገው ሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ በመነጠል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን እርምጃ በመደገፍ ከመንግስትና ከሰራዊቱ ጎን እንደሚቆሙ በአቋም መግለጫቸው አስታውቀዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.