Fana: At a Speed of Life!

በጌዲኦ ዞን በ50 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመረቀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በጌዲኦ ዞን ዲላ ከተማ በ50 ሚሊየን ብር ወጪ በግለሰብ የተገነባው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመረቀ።
በ2 ሺህ ካሬሜትር ላይ ያረፈው ሠላም መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጌዲኦና አጎራባች አከባቢዎች ረዥም እርቀት ተጉዘው የሚያገኙትን ህክምና ያስቀራል ነው የተባለው፡፡
ሆስፒታሉ በዘመናዊ የሕክምና መሳሪያ የታግዘና የተደራጀ እንዲሁም ከ74 በላይ ቋሚ ሰራተኞችን የያዘ ሲሆን የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን በስፔሻሊስት ሐኪሞች እየሰጠ ይገኛል።
ሆስፒታሉ ባለቤት ዶክተር ጌታቸው መርጊያ በ1999 ዓ.ም በክሊኒክነት ተጀምሮ አሁን እስካለበት ደረጃ ድረስ በርካታ ውጣውረድ ማሳለፉን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሕክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ በበኩላቸው ÷በሀገር ደረጃ መከላከልን መሠረት ላደረገው ፖሊሲ የጤና ተቋማት ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ ትልቁ መፍትሔ መሆኑን ገልፀው ለዚሁ እቅድ የግል ባለሀብቶች ተሳትፎ የላቀ እንዲሆን መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የደቡብ ክልል የግል ጤና ተቋማት ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ አባቢ ደግሞ የጤና ሽፋን አገልግሎት እንደ ሀገር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ቢያሳይም በመንግሥት ብቻ የተሳካ ማድረግ ስለማይቻል የግል ባለሀብቶች ተሳትፎ ሊበረታታ እንደሚገባ አሳስበው ለዚህም አመራሩ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።
በመለሰ ታደለ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-

https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.