Fana: At a Speed of Life!

በግድቡ ላይ በካርቱም የተካሄደው ድርድር ውጤታማ ሆኖ መጠናቀቁን ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዳሴ ግድብ ላይ በካርቱም ሲካሄድ የሰነበተው 3ኛው ዙር የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች ድርድር ውጤታማ ሆኖ መጠናቀቁን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ገለፁ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በድርድሩ ውጤት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም አብዛኛው ጉዳዮች ላይ ሀገራቱ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ግብፅ አቅርባው የነበረው “40 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይለቀቅ፤ የአስዋን ከፍታ ከ165 ሜትር ዝቅ አይበል” የሚለውን የቀደመ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ በመተው ሃሳቧን ቀይራለች ብለዋል።

ይህንን ሀሳብ ግብፅ መተዋ ትልቅ ውጤት መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የጠቆሙት።

ግብፅ ያቀረበችው አዲስ ሃሳብ የአባይ ወንዝ ተፈጥሯዊ ፍሰቱ ይጠበቅ የሚል ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ይህንን ሀሳብ እንዳልተቀበለች፤ ተፈጥሯዊ ፍሰቱ ከተጠበቀ የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራትን የመጠቀም መብት ይገታል የሚል አመክንዮ በማቅረቧም ግብጽም ላስብበት ብላለች።

የድርቅ ትርጓሜ ላይ በተነጋገሩበት ወቅት፥ የድርቅ ትርጓሜ ኢትዮጵያ ከ35 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜተር በታች ውሃ ሲፈስ ነው ስትል፥ ግብጽ ደግሞ ከ40 ቢሊዮንኪዩቢክ ሜትር በታች ይሁን ማለታን ተከትሎ ሳይስማሙ ቀርተዋል።

ከዚያ ባለፈ በድርቅ ወቅት ምን ያህል ውሃ ይለቀቅ ከግድቡ ከፍታ ምን ያህል ዝቅ ተብሎ ይለቀቅ በሚለው ላይም ከስምምነት አልተደረሰም።

በቀጣዩ የፈረንጆቹ ጥር 8 እና 9 ቀን 2020 በአዲስ አበባ በሚካሄደው ስብሰባ ከስምምነት ይደረስባቸዋል ተብሎ ይታመናል ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፥ ካልተስማሙ አንቀጽ 10 በስምምነት ይተገበራል ብለዋል።

“ሚኒስትሩ ከቴክኒክ ኮሚቴው ጋር አልተስማሙም” በሚል በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የወጣው መረጃም ሙሉ በሙሉ ሀሰት ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ አንቀጽ 10 የሚተገበር ከሆነ የምንወስደውን አማራጭ መንግስትን አማክረን እንወስናለን ነው ያሉት።

ሀገራቱ በካርቱም በመሪዎች ደረጃ የተፈራረሙት የስምምነት መርሆዎች አካል የሆነው አንቀፅ 10 ሰላማዊ የግጭት አፈታትን የተመለከተ ነው።

ሶስቱ ሀገራት በስምምንቱ አተረጓጎምና አተገባበር ላይ በቅን ልቦና ላይ ተመስርተው በውይይት እና በድርድር ካልተስማሙ ሶስተኘ ወገን አሸማጋይ መጠየቅ ይችላሉ ይላል።

አልያም ጉዳዩ በመሪዎች ደረጃ እንዲታይ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተጠቅሶበታል።

ይህንንም አንቀፅ ለመተግበር የሶስቱም ሀገራት ስምምነትን ይጠይቃል።

 

በባሃሩ ይድነቃቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.