Fana: At a Speed of Life!

በግድቡ ዙሪያ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ውዥንብሮችን ለማጥራት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚፈጠሩ ውዥንብሮችን ለማጥራትና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር አስፈላጊው ርቀት ድረስ ይኬዳል ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሕዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት ዙሪያ አወዛጋቢ ትችት ሰንዝረዋል።

ይህን ተከትሎም የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት “በምንምና በማንም ካሰብነው መንገድ አንቀርም፤ ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም” የሚል አቋም የያዘ መግለጫ አውጥቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተናገሩት ንግግር ተገቢነት የሌለውና ሊሆን የማይችል ነው።

መንግስት በዚህ ጉዳይ የማያወላውል ግልጽና ጠንካራ አቋም አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በውጪውም ዓለም ለማስከበር በዋናነት በየሃገራቱ የሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም የተለያዩ አጋር ተቋማት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የማጠናከር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አክለዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓ፣ በእስያና በሰሜንና በላቲን አሜሪካ ጭምር የኢትዮጵያን ጥቅም ሊያስከብር በሚችል ሁኔታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በግድቡ ዙሪያ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በመስራት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ግድቡ በሚገባ እንዲያውቅና ዓላማውንም እንዲረዳ ለማድረግ ብሎም የሚፈጠሩ ውዥንብሮችን ለማጥራት አሁንም ስራዎች ይሰራሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.