Fana: At a Speed of Life!

በግጭት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው- የገንዘብ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

“በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት”ለባለድርሻ አካላት ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው÷ መንግስት ፕሮጀክቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ በትኩረት እየሰራ  ይገኛል፡፡

የልማት አጋሮች፣ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚመለከታቸው የክልል ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ፕሮጀክቱን ይፋ ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ÷መንግስት በግጭት የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግስት ከግጭቱ ማግስት ጀምሮ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የዕለት ደራሽ እርዳታ በማቅረብ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ፣ በ2014 በጀት ዓመት ለመልሶ ማቋቋም የ5 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት በመመደብ እንዲሁም በ2015 በጀት ዓመት የ20 ቢሊየን ብር በጀት በመመደብ የመልሶ ማቋቋም ሂደቱ ውጤታማ አንዲሆን በትጋት ሲሰራ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ ሁለት የትኩረት አቅጣጫዎች ጉዳት የደረሰባቸውን የህዝብ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባትና ማሻሻል እንዲሁም ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለደረሰባቸው ወገኖች ዘርፈ ብዙ አገልግሎትና ድጋፍ መስጠት መሆኑን አቶ አህመድ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በከፊል ኦሮሚያ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ  ተመልክቷል፡፡

የዓለም ባንክን ጨምሮ የተባባሩት መንግስታት የፕሮጀክት አገልግሎት ቢሮ፣ የተባባሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት እንዲሁም ሌሎች የሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉም ብለዋል፡፡

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ተወካይ ሚስተር ኦስማን ዲዮን በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን የዓለም ባንክ ከዚህ በፊት ያደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ አንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.