Fana: At a Speed of Life!

በጎርፍ ለተፈናቀሉ እና ለተጎዱ ዜጎች በሚሰጠው ምላሽ ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጎርፍ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ዜጎች እየተሰጠ ባለው ድጋፍ ላይ የተስተዋሉ የቅንጅትና የአቅም ክፍተቶችን በመፍታት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ።
ክረምቱ እስኪያልፍ ድረስ የጎርፍ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ተነግሯል።
ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከተፋሰስ ልማት ባለስልጣን ጋር ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በተያዘው ክረምት እስካሁን ድረስ ከ1 ሚሊየን 95 ሺህ በላይ ዜጎች በጎርፍ አደጋ ተጎድተዋል።
ሌሎች ከ313 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ ከቄያቸው ተፈናቅለዋል።
ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት በተያዘው የክረምት ወራት በጎርፍ ምክንያት 2 ሚሊየን ዜጎች እንደሚጎዱና ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ይፈናቀላሉ ተብሎ ታስቦ ነበር።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመነ ዳሮታ እንዳሉት ጎርፍ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የመከላከል ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
የጎርፍ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ግብረኃይል ተቋቁሞ ወቅታዊ መረጃ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ መደረጉንና አሁንም መቀጠሉን ጠቁመዋል።
“ዘንድሮ ከበድ ያለ የጎርፍ አደጋ ቢከሰትም በተከናወኑ የቅድመ መከላከልና የህይወት አድን ሥራዎች እስካሁን ድረስ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ለማድረግ ተችሏል” ብለዋል።
ለተጎጂዎች ድጋፍ በአፋጣኝ ለማድረስም ከዚህ ቀደም ሦስት የነበሩት ማዕከላዊ መጋዘኖች ቁጥር ወደ ስምንት እንዲያድጉና በመጋዘኖች የመጠባበቂያ ክምችት እንዲኖር መደረጉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የክልልና የፌደራል መንግስት ከሚያደርጉት እገዛ በተጨማሪ በየአካባቢው ማህበረሰቡ ተጎጂዎችን እየደገፈ መሆኑንም ገልፀዋል።
ይሁንና በአንዳንድ አካባቢዎች በቂ አቅርቦት ቢኖርም በቅንጅትና በአቅም ችግር ምክንያት ለተጎጂዎች በአፋጣኝ ድጋፍ በማድረግ በኩል ክፍተት መፈጠሩን አስረድተዋል።
ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ለእዚህም በአፋር የደረሰውን መሰል ችግር ለመፍታት የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል በአካባቢው መቋቋሙን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
“ማዕከሉም ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት ያስችላል” ብለዋል ።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችም የተስተዋለ መሰል ችግር መኖሩን ገልፀው፣ በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ የመለየት፣ የማዳረስና የጎደለ አቅርቦት ካለ የማሟላት ሥራ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
“የዘንድሮው ክረምት ከባድ ቢሆንም ግድቦች ከመለቀቃቸው በፊት በዙሪያ ያሉ ሰዎች ቀድመው አካባቢያቸውን እንዲለቁ በመደረጉና በወንዞች ዳርቻ በተሰራው ሥራ ጉዳቱን መቀነስ ተችሏል” ያሉት ደግሞ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ ናቸው።
በዘላቂነት ችግሩን ለመከላከል የውሃ አካላትን ለልማት ማዋልና ግድቦችን መገንባት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፣ ባለስልጣኑ ተፋሰሶች በአግባቡ እንዲተዳደሩና የውሃ ደህንነት እንዲጠበቅ ጥናት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.