Fana: At a Speed of Life!

በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ አስቸኳይና ዘላቂ ተግባራት ተለይተው እየተሰሩ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2013(ኤፍ.ቢ.ሲ) በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ አስቸኳይና ዘላቂ ተግባራት ተለይተው እየተሰሩ መሆኑን ተገለፀ።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የጎርፍ አደጋ በሚመለከት የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት በኢትዮጵያ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ በአምስት ክልሎች በሚገኙ 23 ዞኖች ላይ ጎርፍ ተከስቷል ብለዋል።

በዚህም 580 ሺህ ዜጎች የጎርፍ አደጋ የተጋረጠባቸው ሲሆን እስካሁንም 217 ሺህ ዜጎች በጎርፉ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

በተለይ በታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች ላይ የጎርፍ አደጋው በስፋት መከሰቱንም ገልጸዋል።

በጎረፉ ዜጎች ለከፋ ችግር እንዳይዳረጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ከአጭር ጊዜ መፍትሄ አንፃር ደራሽ ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች አደጋው ለደረሰባቸው ዜጎች እየቀረቡ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በጎርፉ ምክንያት ወረርሽኝና ሌሎች የጤና ችግሮች እንዳይከሰቱ በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሁለት ሄሊኮፕተሮችንና ጀልባዎችን በመጠቀም በጎርፍ የተከበቡ ዜጎችን የማውጣት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ እስካሁን ጎርፉ ከባድ ጉዳት እያስከለ ቢሆንም የሰው ህይወት ግን አልጠፋም።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢኒጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው በበጋው ወቅት በአዋሽ ተፋሰስ ብቻ 136 ሚሊየን ብር በማውጣት 130 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የጎርፍ ጥበቃ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ይህን በማድረግ ይደርስ የነበረውን ጉዳት መቀነስ መቻሉን ነው ያወሱት።
ከአጭር ጊዜ መፍትሄ አንጻርም በቀጣዩ የበጋ ወቅት መሰል የጎርፍ መከላከል ስራ ተጠናክሮ እንሚቀጥል አብራርተዋል።

የጎርፍ አደጋውን በዘላቂነት ለመከላከል ስትራቴጂካዊ እቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ አንጻር ወደ አዋሽ ተፋሰስ በሚገባው የሎጊያ ወንዝ ላይ አነስተኛ ግድብ ለመስራት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

በወንዙ ላይ የሚሰራው ግድብም ለመስኖ ስራ ይውላል ነው ያሉት።

በላይኛውና በመካከለኛው የአዋሽ ተፋሰስ ላይም ውሃን ማቀብ የሚችሉ ግድቦችን ለመስራት የሚያስችሉ ጥናቶችና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይ የቆቃ ግድብ ሲሞላ ወደ ዝዋይ ሃይቅ በማፋሰስ በመጥፋት ላይ ያለውን የአብያታ ሃይቅን መታደግ ይቻላል ብለዋል።

ከክልሎች ጋር በቅንጅት በመሆን የተጠናከረ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ለማበጀት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስተሩ ገልጸዋል።

“በዘንድሮ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ መያዙ ሱዳን አሁን ከገጠማት የባሰ አስከፊ ጎርፍ እንዳይገጥማት አድርጓል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ይህም ኢትዮጵያ ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ያለውን ጠቀሜታ አስመልከታ በተደጋጋሚ ስታራምደው የነበረውን አቋም ትክከልኛ መሆኑን ያረጋገጠ እንደሆነም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.