Fana: At a Speed of Life!

“በጎነት ለአብሮነት” የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 4ኛ ዙር ሰልጣኞች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአራተኛ ዙር “በጎነት ለአብሮነት” የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኞች የምረቃ መርሐ ግብር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ፡፡

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ላለፉት 22 ቀናት የሕይወት ክህሎት፣ የአካል ብቃትና የአመለካከት ብስለትን የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን ሲከታተሉ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ገመቺሳ ኢትቻ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት÷በጎነት ለአብሮነት ወጣቶች ኢትዮጵያዊ መርሆችና ዕሴቶችን በማጎልበት ለሰላም ግንባታ የበኩላቸውን የሚያበረክቱበት ፕሮግራም ነው።

በአካልና በአዕምሮ ብቁና ተወዳዳሪ ወጣቶች መፍጠር የስልጠናው ዋነኛ አለማ መሆኑን ጠቁመው÷ለተመራቂ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው÷ ሰላም ከሁሉም ነገር በላይ ነው፤በተፈጥሮ የተሰጠንን ጸጋ ለመጠቀም ሰላም ከምንም ነገር በላይ ያስፈልገናል ብለዋል።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው አገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የተመረቁት 536 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሁሉም የአገራችን ክፍሎች በመሰማራት ለቀጣይ 10 ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ መሆኑን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ ሰላም ሚኒስቴር ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር “በጎነት ለአብሮነት” በሚል መሪ ቃል ለ4ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 300 በላይ በጎ ፈቃድ ወጣቶች በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ÷ ወጣቶች ከስልጠና በኃላ እየተሸረሸረ የመጣውንየሰላም ችግር በመቅረፉ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል ፡፡

በስልጠና ላይ የቆዩ ወጣቶች በጎ አእምሮና ስነ ልቦና ይዘው ህዝቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ የሰላም ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሂሩት ዴሌቦ ተናግረዋል።

በጀማል ከዲሮ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.